የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ስር የነበሩ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲደራጁ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ወሰነ

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር የነበሩ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲደራጁ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ወስኗል።

በአዲስ ክልል እንዲደራጁ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ ተቀብሎ የወሰነላቸውም የወላይታ ዞን፣ የጋሞ ዞን፣ የጎፋ ዞን፣ የደቡብ ኦሞ ዞን፣ የጌዴኦ ዞን፣ የኮንሶ ዞን፣ እንዲሁም የደራሼ ልዩ ወረዳ፣ የአማሮ ልዩ ወረዳ፣ የቡርጂ ልዩ ወረዳ፣ የአሌ ልዩ ወረዳ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

አዲስ የሚመሰረተው ክልልም ”የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የሚል ስያሜ እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ በሆነ መልኩ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅና የሕዝብ ውሳኔው ውጤት ሪፖርት ለምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የሕዝብ ውሳኔው ሂደትም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የሕዝብን ሰፊ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ የወሰነ ሲሆን ውሳኔው በ5 ተቃውሞና በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

በሌላ በኩል ቀሪዎቹ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር የሚገኙ የሀድያ ዞን፣ ሀላባ ዞን፣ ከንባታ ጠንባሮ ዞን፣ ጉራጌ ዞን ስልጤ ዞን እና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ ክልል እንደሚቀጥሉ የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በዛሬው ዕለት ባካሄደው ሁለተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነው፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW