የፕሬዝዳንት ትራምፕ ካቢኔ አባላት በፈቃዳቸው ሥልጣን እየለቀቁ ነው

ከመላው ዓለም ውግዘት እየደረሰባቸው ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዋሽንግተን ውስጥ የተከሰተውን ግርግር ተከትሎ የካቢኔ አባላት በፈቃዳቸው ሥልጣን እየለቀቁ ነው።

ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው የመንግሥት መቀመጫ እና የሁለቱ ምክር ቤቶች አዳራሾች የሚገኙበትን ካፒቶል ሒል ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ በርካታ የዓለም መንግሥታት ዶናልድ ትራምፕን አውግዘዋል።

የቅርብ ወዳጃቸው ናቸው የሚባሉት የታላቋ ብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጭምር ጠንካራ ቃላትን ተጠቅመው የትራምፕን እንዝላልነት ተችተዋል። በእንዲህ ዓይነት ሁነቶች ዝምታን የሚመርጡት የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርክልም ትራምፕን ወቅሰዋል።

የዴንማርክ፣ የኖርዌይ እና የፈረንሳይ መሪዎችም በካፒቶል ሒል የታየውን ነውጥ ተችተዋል።

ከዓለም መንግሥታት ትችት በተጨማሪ ትናንት ሐሙስ ምሽት ሁለት የትራምፕ የካቢኔ አባላት ሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ተሰምቷል።

የትምህርት ሚኒስትር ቤትሲ ዴቫስ ከሰዓታት በፊት መልቀቂያ አስገብተዋል።
ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት ሚስስ ቤትሲ ዴቫስ በመልቀቂያቸው ዶናልድ ትራምፕ የወንበዴዎችን አመጽ በማቀጣጠል እና ይሁንታን በመስጠት ወንጅለዋቸዋል።

ከሳቸው ቀደም ብሎ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ኤሌይን ቻዎ ሥልጣን ለቅቀዋል። “በሆነው ነገር ስለተረበሽኩ ከትራምፕ ጋር ለመሥራት እቸገራለሁ” ብለዋል በመልቀቂያቸው።

ከካቢኔ አባላት በተጨማሪ የትራምፕ ልዩ ረዳቶቻቸውም መልቀቂያ እያስገቡ ነው።

በዲፕሎማሲ መስክ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ማልቨኒ እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነት መኮንኖች እና የቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ረዳቶችም በብዛት ለቅቀዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ ደግሞ ትራምፕ ለአሜሪካ አይመጥኑም ማለታቸውን ተከትሎ ከሥራ ተሰናብተዋል።

ይህንን ውግዘት ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊ የሥልጣን ርክክብ አደርጋለሁ ብለዋል። ይህን ያሉት ደጋፊዎቻቸው ካፒቶል ሒልን ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ በደረሰባቸው ዓለም አቀፍ ውግዘት ነው።

ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋር የትዊተር ሰሌዳቸው የተመለሰላቸው ዶናልድ ትራምፕ ከዓለም መሪዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከፍተኛ ውግዘት ከደረሰባቸው በኋላ መሸነፋቸውን በግልጽ ቋንቋ ባያምኑም የሥልጣን ርክክቡ ግን ሰላማዊ ይሆናል ብለዋል።

ዲሞክራቶች በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ለማስረከብ 13 ቀናት ቢቀሯቸውም አሁኑኑ ከቤተ መንግሥት እንዲባረሩ ጥያቄ እያቀረቡ ነው።

ሽግግሩ ሰላማዊ ይሆናል ብለው የተናገሩት ትራምፕ ይህ ንግግራቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈታቸውን ዋጥ ያደረጉበት ነው ተብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ በባይደን የተሸነፍኩት ምርጫው ተጭበርብሮ ነው ብለው ያምናሉ።

ሆኖም ለዚህ ክሳቸው አንድም ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም ተብሏል። ተጭበርብሯል ያሉባቸው የግዛት ምርጫ ጣቢያዎች ሁሉ ትራምፕ ያቀረቧቸው ማስረጃዎች በፍርድ ቤት ጭምር ውድቅ ተደርገውባቸዋል።

ሆኖም ዶናልድ ትራምፕ አሁንም ቢሆን የምርጫውን ውጤት በጸጋ መቀበል ተስኗቸዋል።

(ምንጭ፡-ቢቢሲ)