ዩኒቨርሲቲው ለአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ስኬታማነት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ስኬታማነት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ባለፈው ዓመት በነበረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ከ100 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሚዛናዊነት እንዲጠበቅ እና ዘላቂ ልማት እንዲመጣ ለአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀገር የተያዘው ሶስተኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር “ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል በደቡብ ክልል ደረጃ ለማስጀመር በክልሉ የሚገኙ የዘጠኙም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የክልልና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የችግኝ ተከላ በነገው ዕለት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ችግኞችን መትከል ብቻውን በቂ ባለመሆኑ አስፈላጊውን እንክብካቤና ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ተነግሯል፡፡

የወላይታ ሶዶ ኒቨርሲቲ ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ችግኞችን ለተከላ ያዘጋጀ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የአቮካዶ፣ ማንጎና የፓፓያ ችግኞች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

(በመማር ይበልጣል)