የሀገር መከላከያ ሠራዊት በፈጸመው ጀብድ ኢትዮጵያን ከአደጋ ማዳን ተችሏል – ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – የሀገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በፈጸመው ጀብድ ኢትዮጵያን ከአደጋ ማዳን ተችሏል” ሲሉ በመከላከያ ሚኒስቴር የግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ገለጹ፡፡
በመከላከያ የጤና ዋና መምሪያ ከምክትል አስር አለቃ እስከ ኮሎኔል ድረስ ያሉ ማዕረጎች ለ39 አባላትና አመራሮች የማእረግ እድገት ተሰጥቷል።
በመከላከያ ሚኒስቴር የግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ፤ በህግ ማስከበር ወቅት የመከላከያ የጤና ባለሙያዎች ከሰራዊቱ ጎን በመሆን የህክምና እርዳታ በመስጠት ያሳዩት ታታሪነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
“በትግራይ ክልል መቀሌ የነቆጠው የጁንታው ቡድን ኢትዮጵያን መምራት ወይ መበተን በሚል ዓላማ የከፈተብን ጦርነት በማይታመን የውጊያ አፈጻጸም ተከናውኗል” ብለዋል።
የሃገር መከላከያ ሰራዊት በፈጸመው ጀብድ አገርን ማዳን መቻሉን የገለጹት ሌተናል ጀነራል ባጫ፤ “አገራችንን ከጥፋት ማዳን በቻልንበት ማግስት ማዕረግ የተቀበላቹ መሆኑ ትልቅ ዕድለኞች ናችሁ” ብለዋል።
በቀጣይ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የምታካሂድ በመሆኗ ግድቡን የመጠበቅና የሰራተኞቹን ደህንነት ማረጋገጥ የሰራዊቱ ዋነኛ ሃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሰራዊቱ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመከላከያ ጤና መምሪያ ሃላፊ ሜጀር ጀነራል ጥጋቡ ይልማ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት የማእረግ እድገት ያገኙ አባላት ፈታኝ ተልዕኮ የፈጸሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
“ከግንባር እስከ ደጀን በሆስፒታል በሙያቸውና በአመራር ሰጭነታቸው ሃላፊነታቸውን የተወጡ ሁሉ ለሰራዊቱ ደጀን የነበሩ ናቸው” ብለዋል፡፡
የማዕረግ እድገት ያገኙ የሰራዊቱ አባላት በህግ ማስከበሩ ወቅት አስቸጋሪ ወቅቶችን አልፈው ለዚህ ድል በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
የተሰጣቸው ማዕረግ ለበለጠ ሃላፊነት የሚያዘጋጃቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡