ያለፉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ

ያለፉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ 

በቴዎድሮስ ሳህለ

መጋቢት 23/2015 (ዋልታ) ዲፕሎማሲ በአገራትና መንግሥታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የሚካሄድ ዘርፈ ብዙ የውጭ ግንኙነቶች የሚከወኑበት ሁነኛ ጥበብ ነው። የዲፕሎማሲ ዋና ተግባር በአገራት መካከል ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ማስተዳደር እና ሰላማዊ ግንኙነትን ማረጋገጥ ሲሆን የንግድ ስምምነት ድርድሮችን፣ በጋራ ችግሮች ዙሪያ ውይይትን፣ አዳዲስ ፖሊሲዎች መተግበርን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ያካትታል፡፡ ኢትዮጵያም የሺ ዓመታት ዲፕሎማሲ ልምድ እንዳላት አገር ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ስትጠቀምበት ቆይታለች፡፡

በኢትዮጵያ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት የገጠሟትን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቋቋም፣ ኢኮኖሚያዊ ግቦቿን ለማሳካት፣ ከአገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ዲፕሎማሲን በሰፊው እየተጠቀመች ነው፡፡ በዚህም በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶች ተከስተዋል፡፡ በዘርፉ የውጭና የውስጥ ተግዳሮቶችን በመቋቋም በርካታ ውጤታማ ስራዎች ተሠርቷል፡፡ ለዘህም ውጤት ለውጡን ተከትሎ መንግስት በውጭ ግንኙነት ዙሪያ የወሰደው የፖሊሲ፣ የአሰራር እና የአቅጣጫ እርምጃዎች ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም፡፡

በአምስት ዓመታት ዓበይት ተግባራት እና ሁነቶች መካከል በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መድረክ ግንኙነት እንዲሁም በሌሎች ውጤታማ ተግባራት እንደተከናወኑ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ ህግን በማስከበር ዘመቻ ወቅት ከምዕራቡ ዓለም እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የገጠማት ጫና እና እጅ ጥምዘዛ፣ የህዳሴው ግድብ ድርድር እና ተያያዥ ሁነቶችም ከፍትኛ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳቡ ዲፕሎማሲያዊ ትግል የተካሄደባቸውና ኢትዮጵያ በአሸናፊነት የተወጣችባቸው ዓመታትም ነበሩ፡፡

የሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት በወሰደው እርምጃና ቁርጠኛ አመራር የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንዲፋጠን አድርጎታል፡፡ የግድቡን መፋጠን ተከትሎ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከግብፅ እና ሱዳን ጋር ተከታታይ ድርድሮች ተደርገዋል፡፡ በተደረገውም እልህ አስጨራሸ የድርድር ሂደቶች ኢትዮጵያ በአሸናፊነት እየተወጣች መገስገሷ ትውልድ የማይረሳው ህያው ከስተት ነው፡፡ ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. 2015 በሦስቱም አገራት የተፈረመውን የመርህ ስምምነት (Declaration of Principles) መሰረት በማድረግ ግንባታውን ለደቂቃም ሳታቆም ቀጥላለች፡፡ በሦስት ዙር የውሃ ሙሌት በድል አጠናቃ ወደ አራተኛው እየተንደረደረች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያትና መድረኮች በተደረጉ ድርድሮች የናይል ተፋሰስ ሀገራት ከግብፅ እና ሱዳን በስተቀር ውሃውን በፍትሃዊነት እና የጎላ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ መጠቀም የሚለውን መርህ መሰረት በማድረግ ከጎኗ እንዲቆሙ ማድርግ ችላለች፡፡ ጉዳዩንም “ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል መርህ የድርድር ሂደቱ ከአፍሪካዊ ተቋም እና አፍሪካዊያን እጅ እንዳይወጣ በማድረግ በአደራዳሪነት ስም ገብተው ጉዳዩን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊመሩ የቋመጡ አካላትን ኩም አድርጋለች፡፡

ቀጣዩ የድርድር ሂደትም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ውሃ አጠቃቀም መርህን እና ህግን በተከተለ መንገድ በአፍሪካዊያን እና አፍሪካዊ ተቋም ብቻ እልባት እንዲገያኝ ፈር አሲዛዋለች፡፡ ይህ በርካታ ዓመታት የተለፋበት ታላቅ የዲፕሎማሲ ድልና ህያው የትውልዶች ቅብብል ታሪክ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋነኛው አእማድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም አገሪቱ የኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቿን በዓለም አቀፍ ግንኙነት መድረክ ለማሳካት የምትችልባቸውን ልዩ ልዩ ተግባራት ስትከውን ቆይታለች፡፡ የውጭ መዋዕለ ነዋይ በሰፊው ለመሳብና ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት የማሳደግ ዋነኛ ግቧና መርህ አድርጋ ወደ ሥራ በመግባቷ ውጤት እያስመዘገበችበት ነው፡፡

ይህን ለማሳካት ፖሊሲ ነድፎ ሳቢ እና አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡ የግብር እፎይታ፣ ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ እና ሌሎች መደላድሎችን የማዘጋጀት ጥረት ተደርጎ የውጭ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያለሙ ስራዎች በመሰራታቸው በርካታ ኢንቨስተሮች በአገራችን በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡

በቅርቡ እንኳን የፓኪስታን፣ የደቡብ ኮርያ፣ የህንድ እና የቱርከዬ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች ጎብኝተው በልዩ ልዩ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳሳዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የአገር ውስጥ ዘርፎችን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ለማድረግ ተጨባጭ ስራዎች በመሰራታቸው የተፈጠረውን ምቹ እና አስቻይ ሁኔታዎች ተጠቅመው አንዳንድ ኩባንዎች ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማራው ሳፋሪኮምም እንደ አብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በታሪክ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፉ የግል ኩባንያ ሲሰማራም የመጀመሪያ ያደርገዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በርካታ ሀገራት የልማት ድጋፍ እና ትብብራቸውን ለመቀጠል ፍላጎት ከማሳዬታቸውም በላይ የፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ቻይና፣ ፊላንድ፣ ስፔን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ኢትዮጵየያን ጎብኝተዋል፤ ልማታዊ ድጋፍ ለማድረግም ስምምነት መፈራረማቸውን የገንዘብ ሚንስቴር በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል፡፡

የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ባንክም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በጦርነት የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸው የኢኮኖሚ ድፕሎማሲ ውጤታማነትን ያሳያል፡፡

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተውን ጦረነት ተከትሎ የተወሰደውን የህግ ማስከበር ሂደት ወደ ራሳቸው ፍላጎት ለመጠምዘዝ ምዕራባዊያን ያደረጉት ጫና ከፍተኛ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በወርሃ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጥቃት ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ የተናበበ ዓለም አቀፍ ጫና ሲደረግባት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ጫናው አሁንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚደረግና ጨርሶ እንዳላቆመ ምልክቶች ይስተዋላሉ፡፡

በተያዘው በአውሮፓዊያን አቆጣጠር መጋቢት አጋማሽ ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ የአውሮፓ ህብረት ለመግለጫው የሰጠው ድጋፍ እንዲሁም ሚዲያዎቻቸው የሚያንጸባርቁት አቋም ላለመቆሙ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

የአገር መከላከያ መጠቃቱን ተከትሎ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር እና ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ ከወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ ከምዕራቡ ዓለም የተናበበ እና ብዙ አካላት የተሳተፉበት ጫና እና ውንጀላ ዶፍ በኢትዮጵያ ላይ ሲያወርዱት ይታያል፡፡ ታላላቆቹ የማህበራዊ ሚድያ ኩባንያዎችም ግጭት አባባሽ መልዕክቶች ሲሰራጩ ዝም ከማለት ባሻገርም የኢትዮጵያ ደጋፊ ድምጾችን በማፈንም በሰፊው ተሳትፈዋል፡፡

ታላላቆቹ ዓለም አቀፍ ሚዲዎች በህግ ማስከበሩ ወቅት መረጃን በማዛባት እና በማሰራጨት እንዲሁም ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን በመልቀቅ ረገድ ሰፊ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለአብነትም የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን. እ.ኤ.አ ግንቦት 12 ቀን 2021 የህወሓት ኃይል አዲስ አበባ ዳርቻ ላይ ደርሷል የሚል የሀሰት ዜና ማሰራጨቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በተለዬ መልኩ አሜሪካ በተናጠል ኢትዮጵያን ለአፍሪካ አገራት ከተሰጠው ከቀረጥ ነፃ የሆነ የገበያ እድል (African Growth and Opportunity Act-AGOA) ተጠቃሚነት እስከመሰረዝ ደረሰ ውሳኔ አስተላልፋለች፡፡

እነዚህን ሁሉ የምዕራባዊያንን ጫና ተቋቁማ እና ጦርነቱም በሠላማዊ መንገድ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መቋጫ እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ያደረገችው የዲፕሎማሲ ጉዞ ፍሬ አፍርቶ የሰላም ስምምነት ለመፈረም በቅቷል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ የተጎናጸፈችው ደማቅ የዲፕሎማሲያዊ ድል ነው፡፡

በአምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ሌላው ውጤት የተዘገበበት ዘርፍ ነው፡፡ በውጭ አገራት በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን በመታደግ እና መብታቸውን በማስከበር ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ተጨባጭ ስራ ተሰርቷል፡፡ በተለይ  በአረቡ ዓለም በተለያዩ አገራት በህገ ወጥ መንገድ ገብተው ሰነድ የሌላቸው እና የታሰሩ ዜጎችን ከአገራቱ ባለስልጣናት ጋር በመወያየት እና ከዓለም አቀፍ ፍልሰት ድርጅት ጋር በትብብር ወደ ሀገራቸው የመመለስ እና እንደገና የማቋቋም ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳስታወቀው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሳኡዲ አረቢያ ብቻ ከ125 ሺሕ በላይ በችግር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያንን መንግሥት ወደ አገራቸው መመለሱ ትልቅ ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ስኬት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በዚህ ዘርፍ በመንግስት እና በዳያስፖራው መካከል ቀድሞ የነበረውን ጥርጣሬ በመቅረፍ የተሸለ ግንኙነት በመፍጠር በአገር ቁልፍ ጉዳዮች ላይ በግንባር ቀደምትነት እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ በህዳሴ ግድብ መዋጮ እና ዘመቻ ዜጎች ሰፊ ተሳትፎ አድርገዋል፤ በህግ ማስከበር ዘመቻውም ድጋፋቸው የጎላ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲም (Multilateral diplomacy ኢትዮጵያ ባልፉት አምስት ዓመታት ውጤት ካስመዘገበችባቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች አንዱ ነው፡፡

የሰሜኑ የህግ ማስከበር ዘመቻን ተከትሎ አገሪቱ አባል ከሆነችባቸው ታላላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች  ከፍተኛ ጫና ገጥሟት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ምንም እንኳን በለውጡ መጀመሪያ አካባቢ በቅርበት ሲደግፍ እና ሲያበረታታ ቢቆይም የሰሜኑ ህግ የማስከበር ዘመቻን ተከትሎ በሁሉም የድርጅቱ ቅርንጫፎች በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያደርግ መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በምዕራባዊያን ፊታውራሪነት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከ16 ጊዜ በላይ ተሰብስቦ የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ ሞክሮ በቻይና እና ሩሲያ ተቃውሞ እና ሌሎች ወዳጅ ሀገራት ድጋፍ እቅዳቸው መና ቀርቷል፡፡

የሰሜኑን የህግ ማስከበር ዘመቻ በሠላማዊ መንገድ ለመቋጨት ኢትዮጵያ ወደ ተግባር ከገባችበትና የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ግን ድርጅቶቹ የአቋም ለውጥ አድርገው በመልሶ ማቋቋም እና ተሃድሶ እንዲሁም በልማት ስራዎች ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት በመልሶ ግንባታ፣ መለሶ ማቋቋም እና ልማት ሥራዎች ዙሪያ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው እየገለጹ ነው፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከኢትዮጵያ ጎን በመሆንም ሆነ ድጋፍ በማድረግ በኩል የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ህብረቱ እና አባል አገራት ለኢትዮጵያ ያልተቋረጠ ድጋፍ ከማድረጋቸው በላይ ህብረቱ የህዳሴው ግድብ ድርድርን አየመራ ይገኛል፡፡ የሰላም ስምምነቱም በህብረቱ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል መርህ ውጤት ላይ ደርሷል፡፡

በደቡብ-ደቡብ ትብብር ማዕቀፍም ሰፊ እና ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ስራ ተሰርቷል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ያልተቋረጠ ጠንካራ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያገኘችው ከደቡባዊ የዓለም ክፍል ካሉ አገራት ልዩ ልዩ የትብብር መድረኮች ነበር፡፡ በዚሁ በባለብዙ ወገን መድረክ ኢትዮጵያ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ትግል አካሂዳ ውጤት አግኝታበታለች፤ በዚህ መስክም አመርቂ የዲፕሎማሲ ድል ያገኘችበት ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ባደረገቻቸው የዲፕሎማሲ ውጣውረዶች ውስጥ አዎንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ውጤታማ ያደረገችበትና አሉታዊ የሆኑ ከውጭና ከውስጥ የተካሄዱ የኢትዮጵያን መንግሥት የማዳከም ብሎም አገርን ለማፍረስ የተቀናጁ ተልዕኮዎችና ፕሮፓጋንዳዎች የከሰሙበት ነበር፡፡

በመሆኑም ዲፕሎማሲው በተለያዩ ዘርፎች በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መድረክ ግንኙነት እንዲሁም በሌሎች ውጤታማ ተግባራት የተከናወነበትና በዓለም መድረክ ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ያለፈችበትና ጫናዎችን በመቋቋም በድል የተሻገረችበት ዓመታት ነበሩ፡፡