“ዶላር እናባዛለን” በማለት የማጭበርበር ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) ቦሌ ክፍለ ከተማ “ዶላር እናባዛለን” በማለት የማጭበርበር ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ኢንተለጀንስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ‘ሲኤምሲ’ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ዶላር እናባዛለን በማለት የአካባቢውን ህብረተሰብ ሲያጭበረብሩ የነበሩ ካሜሮናዊና ኢትዮጵያዊት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ሰዓት ዶላር እናባዛለን በማለት ለማጭበርበሪያ የሚጠቀሙባቸው ሁለት ካርቶን የጦቆረ ዶላር መሳይ ወረቀትና ሁለት ጣርሙስ ኬሚካል ይዘው መገኘታቸው ታውቋል፡፡

ከማህበረሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ሁለቱንም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እየተጣራ ይገኛል ተብሏል፡፡

እንደነዚህ አይነት ህገወጥ ተግባር  በሚፈጽሙ ግለሰቦች ዙሪያ ጥቆማ በመስጠት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአዲስ አበባ  ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡