ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ለተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጡ

ዶ/ር ኢኒጅነር ስለሺ በቀለ

ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ለተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውን ገለፁ።

ሚኒስትሩ ለዋና ፀሀፊው ግንባታው ስላለበት ሁኔታ፣ ስለሁለተኛ ዙር ሙሌት እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ስለሚካሄደው ድርድር ተገቢውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በግድቡ ቴክኒካልም ሆነ ህጋዊ መንገዶች ዙርያ ግልፅ መርህ አስቀምጣ እየተጓዘች መሆኑንም አስረድተዋል።

በግድቡ ዙርያ ለሚነሱ ጉዳዮች ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርህ በመከተል አፍሪካ በራሷ ጥበብ ችግሮቿን ሁሉ መሻገር እንደምትችል ለዓለም ማሳየት ይቻላል የሚል እምነት ኢትዮጵያ እንዳላትም ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የህዳሴውን ግድብ ድርድር ወደ አፍሪክ ህብረት እንዲመለስ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ኢትዮጵያ የጀመረችው ጉዳት የማያስከትለውን የልማት ፕሮጄክት በቅንነት ስለተረዱና ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ስላደረጉ አመስግነዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ፍትሃዊ እና ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ፍጻሚ እንዲያገኝ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሐሙስ ሀገሬን ወክዬ በጸጥታው ምክር ቤት ውጤታማ ገለጻ አድርጌያለሁ ያሉት ሚኒስትሩ፣ የህዳሴው ግድብ ድርድር በአፍሪካ ህብረት መፍትሔ እንደሚያገኝ እምነታቸው እንደሆነ አስፍረዋል።