ጀርመን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመፍታት እየተወሰደ ያለውን ተግባር እንደሚትደግፍ ገለጸች

ነሐሴ 11/2014 (ዋልታ) ጀርመን በአፍሪካ ሕብረት መሪነት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመፍታት እየተወሰደ ያለውን ተግባር እንደሚትደግፍ ገለጸች፡፡

በጀርመን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ላቲን አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ክርስትያን ባክ (ዶ/ር) ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በወቅቱም በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተረጋጋ እና እየተሻሻለ መሆኑን ያስረዱት አምባሳደሯ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት፣ የሰሜኑን ግጭት በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች፣ ሦስተኛ ዙር የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በድርቅ፣ ጎርፍ፣ ግጭት እና በረሃ አንበጣ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ እና ሶማሌ ክልል ለሚገኙ ወገኖች የሰብአዊ ዕርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ የሚገኙ አገራትን ለመርዳት የሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት የበኩሏን ሚና እየተጫወተች መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

ክርስትያን ባክ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ላለው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ አገር መሆኗን ጀርመን እንደሚትገነዘብ ገልጸው በአፍሪካ ሕብረት መሪነት በሰሜኑ ያለውን ግጭት ለመፍታት እየተወሰደ ያለውን ተግባር አገራቸው እንደሚትደግፍ መሳወቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW