በክልሉ በጦርነቱ ውድመትና ዝርፊያ ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ

ነሐሴ 11/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል በጦርነቱ ውድመትና ዝርፊያ ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት ከ79 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና መሳሪያ እና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን በአሜሪካ የልማት ድርጅት የትራንስፎርም ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው ያደረገው፡፡

የትራንስፎርም ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር ኃላፊ እና የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ አስናቀ እንዳሉት ድርጅታቸው በጦርነቱ ውድመትና ዝርፊያ ያጋጠማቸውን ጤና ተቋማት መልሶ ለማደራጀት ከ234 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

አሁን የተደረገው የ79 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የህክምና መሳሪያዎችና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ የክልሉ ጤና ቢሮን ፍላጎት መሰረት አድርጎ መቅረቡን ጠቁመው ይህም የእናቶችን እና ህጻናት ጤናን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር ማርታ ምንውየለት በበኩላቸው ድርጅቱ በጦርነቱ ውድመትና ዝርፊያ ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ ለማደራጀት የተጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በጦርነቱ የወደሙና የተዘረፉ ጤና ተቋማት በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች ርብርብ መልሶ በማደራጀት ሥራ እንዲጀምሩ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡

ድርጀቱ ጤና ተቋማት ያለባቸውን ችግር ለይቶ ያደረገው ድጋፍ ተቋማቱን መልሶ በማደራጀት ለሚደረገው ርብርብ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት ኃላፊው ሌሎች አጋር ድርጅቶችም እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡