ሚያዝያ 29/2015 (ዋልታ) ግብርናን በቴክኖሎጂ ማዘመን የዚህ ዘመን ትውልድ የቤት ስራ መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳይንስ ሙዚየም “በስንዴ የተገኘውን ስኬት በሌሎችም ምርቶች መድገም” በሚል መሪ ቃል ባስጀመሩበት የፓናል ውይይት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ግብርና የእድገት ምንጭ፣ የኑሮ መሰረት እና የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል።
በዚህ ልክ የምንፈልገውን ሴክተር ማዘመን ያስፈልጋል፤ ግብርና በምንፈልገው ልክ የሚሰጠን በምንሰጠው ትኩረት ልክ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ቀደመው ጊዜ የዝናብ ወቅትን ብቻ እየጠበቁ ግብርናን ማስኬድ አይቻልም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብርናውን በሜካናይዜሽን እና በሌሎችም ቴክኖሎጂዎች መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ይህም የዘመኑ ትውልድ የቤት ስራ ነው ብለዋል።
መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ በርካታ ውጤቶች እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው በስንዴ ምርት የተገኘውን ውጤት ለአብነት አንስተዋል።
በስንዴ የተገኘውን ውጤት በሌሎችም ምርቶች መድገም እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ በተለይ እንደ አፈር አሲዳማነት ያሉ ችግሮችን መፍታት፣ የገጠር ስራ ፈላጊውን አቅም ማሳደግ፣ የግብይት ስርዓቱን ከግብርናው ጋር የማመጋገብ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የምርምር ፈጠራዎች ዐውደ ርዕይ ላይ የቀረቡ የቴክኖሎጂና ምርምር ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የፓናል ውይይቱ በስንዴ ልማት የተገኘውን ስኬት በሌሎች ምርቶች ለመድገም ተሞክሮ የሚወሰድበት፣ ግብርናውን በቴክኖሎጂ ለማዘምን የሚያስችሉ አሻጋሪ ሀሳቦች የሚንፀባረቁበት እና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት እንደሆነም ተጠቁሟል።
በትዕግስት ዘላለም