ሶሪያ ወደ አረብ ሊግ አባልነት ተመለሰች

ሚያዝያ 29/2015 (ዋልታ) የአረብ ሊግ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሶሪያን ከሊጉ አባልት ያገደበትን ውሳኔ በመቀልበስ ወደ አባልነት መመለሱን አስታወቀ፡፡

ሶሪያ በፈረንጆቹ 2011 የአረብ የጸደይ አቢዮትን ተከትሎ በተነሳ አመጽ እና እሱን ተከትሎ በፈነዳው የእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ሊጉ ከአባልነት አግዷት እንደነበር ይታወቃል፡፡

የሊጉ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ካይሮ ላይ ተሰብስበው የሶሪያን አባልነት መልሰው ያጸደቁ ሲሆን ይህም ከ12 ዓመታት እግድ በኋላ ወደ ሊጉ እንድትመለስ እስችሏታል፡፡

ወደ አባልነት እንድትመለስ የወሰነው ሊጉ ግንቦት 19/2023 በሳዑዲ አረቢያ ከሚያደርገው ስብሰባ ቀደም ብሎ ነው፡፡

የአረብ ሊግ ዋና ጸሓፊ አቡል ገይጥ የሶሪያን ወደ ሊጉ የመመለስን ውሳኔ ተከትሎ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ወደ አባልነቷ ስለተመለሰች ፕሬዝዳንቱ በሊጉ ስብሰባ መሳተፍ ይችላል ብለዋል፡፡

ወደ ሊጉ የመመለሱ ውሳኔ የተፋጠነው ሶሪያ ባለፈው የካቲት ወር በከባድ ርዕደ መሬት ከተመታች በኋላ እና በቻይና አደራዳሪነት ሳኡዲና ኢራን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ወደ ነበረበት ከመለሱ በኋላ እንደሆነ አልጀዚራ በዘገባው አመልክቷል፡፡

ሁለቱ አገራት በሶሪያ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ የተለያዩ ተዋጊ ቡድኖችን ሲደግፉ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ባለፈው ወር የሳኡዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኢራኑ ፕሬዝዳንት በደማስቆ ጉብኝት ማድረጋቸው የአገራቱ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ማለቱን ያሳያል ነው የተባለው፡፡

የሶሪያ ጉዳይ በአረብ ሊግ ማዕቀፍ መፈታት አለበት የሚል አቋም መያዙንም መረጃው አመላክቷል፡፡