ግብፅ እና ሱዳን ወዳጅነታቸውን የሚያጠናክሩት በኢትዮጵያ ላይ የፕሮፖጋንዳ ጫና ለማሳደር መሆኑ ተገለፀ

መጋቢት 3/2013 (ዋልታ) – ሰሞንኛው የግብፅ እና ሱዳን ወዳጅነታቸውን የማጠናከር ተግባር በኢትዮጵያ ላይ የፕሮፖጋንዳ ጫና ለማሳደር እና ሌሎች የአረብ ሀገራትን ከጎናቸው ለማሰለፍ ያለመ ነው ሲል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚሟገተው ጋዜጠኛ ማሕመድ አልአሩሲ ገለጸ፡፡

የሁለቱ ሀገራት ስምምነት እና ወዳጅነት በኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደር የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ ያለመ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አንድ ሀገር ከሌላ ሀገር ጋር ስምምነት የማድረግ መብት ቢኖራትም ነገር ግን በስምምነት ውስጥ የኢትዮጵያ ስም የሚጠቀስ ከሆነ ጉዳዩ ያገባናል ሲሉም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ችግር ሲከሰት ስለ ሀገራችን ከኛ ባላይ እንደሚያውቋት ነው የሚያወሩት የሚለው ማሕመድ አላሩሲ፣ ኢትዮጵያዊያንን በዘር በመከፋፈል ሀገሪቱን ለመበተን እንደሚሰሩ ያለምንም ህፍረት በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው ማስተጋባት የእለት ተለት ተግባራቸው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

እነዚህ ሀገራት ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ከወትሮው የተለየ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ይፈጥራሉ የሚል እምነት የለኝም ያሉት ማህመድ አላሩሲ፣ ኢትዮጵያውያን ከምንም በላይ የውስጥ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት ግዜ ላይ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
(በአሳየናቸው ክፍሌ)