ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ ክትባት አስጀመሩ

መጋቢት 4/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 እፎይታ ጤና ጣቢያ በመገኘት የኮቪድ-19 ክትባትን በይፋ አስጀመሩ።

ክትባቱን በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ከንቲባዋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከገባ ጀምሮ በሽታውን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ግንባር ቀደም ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የኮቪድ-19 ክትባትም በቅድሚያ ለጤና ባለሙያዎች እንደሚሰጥ የገለፁት ወ/ሮ አዳነች፣ ህብረተሰቡም ክትባቱ እስኪደርሳቸው ድረስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ በበኩላቸው፣ በኮቫክስ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኮቪድ-19 ክትባት በዛሬው ዕለት በከተማዋ በሁሉም ጤና ተቋማት ለሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች፣ በእድሜና ለበሽታው ተጋላጭ ጤና ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ የህብረተሠብ ክፍሎች እንደሚሰጥ ከከተማ አስዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡