ጠንካራ እና ፕሮፌሽናል ሠራዊት ለመገንባት አሠልጣኞች ሞዴል መሆን ይጠበቅባቸዋል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

መስከረም 19/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠንካራ እና ፕሮፌሽናል የመከላከያ ሠራዊት ለመገንባት ወታደራዊ አሰልጣኞች ሞዴል ሆነው መገኘት እንደሚጠበቅባቸው የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፈልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከላትን አመራሮች እና አሰልጣኞች አቅም ለማሳደግ የሰልጥኖ አሰልጣኞች ስልጠና እየተካሄደ ይገኛል።

በኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ እና የልዩ ኃይል ጸረ ሽብር ማሰልጠኛ ማዕከላትን አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ታሳቢ ባደረገው የሰልጥኖ አሰልጣኞች መድረክ ላይ ፈልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተገኝተው ለሰልጥኖ አሰልጣኞቹ ልምድ እና ተሞክሯቸውን አጋርተዋል።

ፈልድ ማርሻል ብርሃኑ ከሠልጥኖ አሰልጣኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ኮማንዶ እና አየር ወለድ የውትድርና ህይወትን ሀ ብለው የጀመሩበት የጦር ክፍል መሆኑን አውስተው ከዛን ጊዜ አንስቶ አሁን እስከ ደረሱበት ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ድረስ የተጓዙበትን የውትድርና ልምድ እና ተሞክሮ ለሰልጣኞቹ ገልጸውላቸዋል።

እንደ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጻ እያንዳንዱ አሰልጣኝ ለሚመራቸው እና ለሚያሰለጥናቸው አባላት አርዓያ እና ሞዴል ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል።

የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ አባላትም በተሰማሩበት የውትድርና ሙያ መስክ ህዝብ እና መንግስት የሚሰጧቸውን ተልእኮዎች በቅንነት እና በታማኝነት መፈጸም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው መከላከያ እንደ ተቋም ተግባራዊ እያደረገ ለሚገኘው ፕሮፌሽናል ሠራዊት ግንባታ ስልጠና የጎላ ድርሻ እንደሚያበረክት የመከላከያ ሰራዊት መረጃ አመላክቷል፡፡