ፋሽስት በወረራ በረገጣት ምድር ለማየት የተፀየፋትን ሰንደቅ አርበኛዉ በሮም አደባባይ ተከላት!
ደም የተከፈለላትን የነፃነት ምልክት ግራዚያኒ በጦቢያ ምድር አልይሽ ሲላት ጀግናዉ አብዲሳ አጋ ግን እዛዉ በሜዳዉ ሮም በሞሶሎኒ ቀዬ ከፍ ከፍ አደረጋት!
ነገሩ እንዲህ ነዉ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ በአራቱም አቅጣጫ የሚገኙ የኢትዮጵያ አርበኞች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነዉ ለሀገራቸዉ ነፃነት መዋደቅ ጀመሩ፡፡
ከነዚህ ጀግኖች አንዱ የፋሽስቱን ጦር እንደ ቋያ እሳት እየለበለበ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣዉ አብዲሳ አጋ ነዉ፡፡
ይህ ኢትዮጵያዊ ጀግና ዘመናዊ መሳሪያዎች ከታጠቀው የጣልያን ጦር ጋር ተፋልሞ በርካታ ድሎችን ካገኘ በኋላ ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ቆይቶ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት የቁም እስረኛ ሆነ።
በኋላ ጣልያን ኢትዮጵያን እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ የጦር እስረኛ ተደርገዉ ወደ ጣልያን አገር ተወሰዱ።
አብዲሳ አጋ ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት እስር ቤት እዛው ታስሮ ከሚገኝ የዩጎዝላቪያ እስረኛ ጋር በጋራ እቅድ በማውጣት ከእስር ቤት ማምለጥ ቻለ፡፡ ከእስር ካመለጡ በኋላ ከፋሺስት ጣልያን ወታደሮች በመደበቅ እና በመሸሽ ፋንታ በአብዲሳ መሪነት በሌሊት ታስረው ወደነበረበት እስር ቤት ተመልሰው ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም የታሰሩትን እስረኞች በሙሉ ነጻ በማውጣት የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ለአለም አስመሰከሩ፡፡ አብዲሳ ከእስር ቤት ያስመለጣቸውን ሰዎች በማሰባሰብ የራሱን ጦር ካደራጀ በኋላ ጣልያኖችን በገዛ አገራቸው መፈናፈኛ አሳጣቸዉ።
ጣልያኖች የአብዲሳን ጦር በፍርሃት ያዩ የነበረ ሲሆን በተለያዩ ቦታዎች ከጣሊያን ጦር ጋር በመዋጋት ብዙ ድሎችን አስመስግቧል። ትግሉን አፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ተቀሰቀሰ።
የአሜሪካ እና እንግሊዝ መንግስታት ከጀርመን ጋር የነበረችውን ጣልያንን እየተዋጉ በነበረ ሰዓት ስለ አብዲሳ ዝና ሰሙ፡፡ ለጦሩ የሚገባውን ድጋፍ በማድረግ የፋሺስት ስርዓቱን ለማዳከም ከሚያግዙ መንገዶች አንዱ ሆኖ አገኙት፡፡ በድጋፉ በመጠናከር ፋሺስቱን ሰራዊት ማርበድበድ የቀጠለው አብዲሳ የጣልያን ጦር ተሸንፎ ዋና ከተማዋ ሮም በአሜሪካ እና እንግሊዝ በሚመራ ጦር እጅ ስር ከወደቀች በኋላ የሚመራቸውን ከተለያዩ አገር የተዉጣጡ ወታደሮች በሙሉ ክንዳቸው ላይ የኢትዮጲያን ባንዲራ እንዲያስሩ በማድረግ የሃገሩን ባንዲራ እያውለበለበ ሮም ከተማ ሲገባ በአለም አቀፉ ህብረት ጦር ትልቅ አቀባበል ተደረገለት፡፡
ይህች ባንዲራ ጀግናዉ አብዲሳ በሀገሩ ጠላት ምድር ያዉለበለባት፣ የአድዋ ጀግኖች የሞቱላት፣ አርበኞች የቆሰሉላት፣ አባቶቻችን ደማቸዉን ያፈሰሱላት አጥንታቸዉን የከሰከሱላት፣ አፍሪካዉያን ብሎም ሁሉም ጥቁሮች የሚመኩባት፣ ዉድ ዋጋ የተከፈለላት የነፃነት ምልክት ናት፡፡ እንጠብቃት!
በሳሙኤል አማረ