በሰንደቅ ዓላማችን ሥር ተሰባስበን የኢትዮጵያን ሕብረብሔራዊ አንድነት እናፀናለን- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ጥቅምት 5/2016 (አዲስ ዋልታ) 16ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች በመላ ሀገሪቱ እየተከበረ ነው።

መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ16ኛ ብሔራዊ የሰንደቅዓላማ ቀን አደረሳችሁ!

የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ የነፃነታችን አርማና የክብራችን መገለጫ ነው፡፡

ሰንደቅዓላማችን ከትውልድ ትውልድ የተሸጋገረ፣ የጀግኖች አባቶቻችን የደማቸው ፍሳሽ፤ የአጥንታቸው ክስካሽ እንዲሁም የመስዋዕትነት ውጤት የሆነ የድል ሰንደቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ፣ የሕዝቦቾን ነፃነትና ክብር ለማጽናት ጀግኖች ኢትዮጵያዊን ለሰንደቅዓማችን ፍቅርና ክብር በአንድነት መስዋትነት ከፍሏል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ለሉዓላዊነታችን የተከፈለ መስዋዕትነት እና ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

የሀገራችን ሉዓላዊነት ምልክት የሆነው የሰንደቅዓላማችን ፀንቶ የቀጠለው ኢትዮጵያዊያን በአንደነት በከፈሉት መስዋእትነት ነው፡፡

ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገርአቀፍ ደረጃ 16ኛው የብሔራዊ ሰንደቃላማ ቀን “የሰንደቅዓላማችን ከፍታ ለሕብረብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

የዘንድሮውን የሰንደቅዓላማ ቀን ስናከብር ሕብረብሔራዊ አንድነታችን ሉዓላዊነታችን እና የህልውናችን ዋስትና መኾናቸውን ታሳቢ ልናደርግ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ሕብረብሔራዊ ሀገር ናት፡፡

እጅግ ብዙ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ መልከአምድርና የአየር ጠባዮች፣ ፍላጎቶች፣ አስተሳሰቦች፣ እምቅ ሀብቶች ያላት ብዝኃነት መገለጫዋ የኾነች ዕፁብ ድንቅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያችን ብዙ ኾና አንድ፤ አንድ ኾና ደግሞ ብዙ ነች፡፡

በዛሬው ዕለት የሰንደቅዓላማ ቀንን ስናከበር እነዚህን ኹለት የሀገራችንን ምሶሶ የኾኑ መገለጫዎች መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሕብረብሔራዊ አንድነታችን ሲጠናከር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትም በፅኑ መሠረት ላይ ይቆማል፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓለማ ክብር ከፍ ይላል፡፡ የሰንደቅዓላማችን ከፍታ በዘላቂነት የሚቀጥለው ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር በሚከናወነው ጠንካራ ሥራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከትላንት እስከ ዛሬ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነፃነት በደማቸው ጠብቆ አቆይቷል፣ ሰንደቅዓላማችንን ከፍ አድርጓል፡፡ የዛሬ ትውልድ በአባቶቹ የህይወት መስዋእትነት ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ የቆየችውን ሀገር በላቡ ማፅናት ይጠበቅበታል፡፡ ዛሬ ላይ ሉዓላዊነታችን በዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው ሀገራችንን ከልመና ነፃ ስናወጣት ነው፡፡

ይህ የሚረጋገጠው ትውልዱ ያለበትን እዳ ተገንዝበው በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ በላቡ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ሲያረጋግጥ ነው፡፡ የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ሲኾን የማንነታችን መገለጫ፣ ሰንደቅ ዓላማችንም ልዕልናው ይጨምራል፡፡

መላው ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችን ሰንደቅዓላማ ያለንን ክብርና ፍቅር ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን ሊያስጠብቁ በሚችሉ ክንውኖች ላይ በመሳተፍ በተግባር ማሳየት ይገባናል፡፡ የሀገራቸውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ መስዋዕትነት የሚከፍሉትን አካላት እንደ ወትሮው ኹሉ በማክበር ለሰንደቅዓላማችን ዘብ መቆማችንን በተጨባጭ ማስመስከር ይጠበቅብናል፡፡

ሕብረብሔራዊ አንድነታችንንና ሉዓላዊነታችንን አፅንተን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ በከፍታ እናውለበልባለን!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት