ፊንላንድ በአማራ ክልል የምታደርገውን የፕሮጀክቶች ትግበራና ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

 

የፊንላንድ መንግሥት በአማራ ክልል የሚያደርገውን የፕሮጀክቶች ትግበራና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቋል።

በኢትዮጵያ የፊንላንድ ኤምባሲ የልማት ትብብር ጉዳዮች ኃላፊ አርቶ ቫልጃስ ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ጋር ትብብራቸውን በሚያጠናክሩበት ጉዳይ ውይይት አድርገዋል።

የፊንላንድ መንግሥት በአማራ ክልል በግብርና፣ በገጠር የንጹህ መጠጥ ውኃና በጤና አጠባበቅ፣ በመሬት አስተዳደርና በትምህርት ዘርፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ያደርጋል።

አርቶ ቫልጃስ እንዳሉት በአማራ ክልል ተግባራዊ እያደረጓቸው ያሉት የልማት ፕሮጀክቶች የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉና ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ናቸው።

በቀጣይም ከክልሉ የ10 ዓመታት ስትራቴጅክ እቅድ ጋር የሚጣጣሙ ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የፊንላንድ መንግሥት በአማራ ክልል ተግባራዊ እያደረጋቸው ያሉ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ናቸው።

የፊንላንድ መንግሥት በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በትብብር እንደሚሠራም ገልጸዋል።
(ምንጭ፡- አብመድ)