በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ሴንተር “የአይኬር ኢኒሼቲቭ” ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ሴንተር የአይኬር ኢኒሼቲቭ ማስጀመሪያ ፕሮግራም መካሄዱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

“አይኬር” ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሆስፒታሎች ለማምጣት፣ ታካሚ ተኮር አገልግሎቶችን ለማጠናከር፣ በተቋም ውስጥና ውጭ ያሉ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በሆስፒታሎች አገልግሎት ዙሪያ ተግዳሮቶችን በመፈተሽ ውጤታማ አሰራሮች ለመዘርጋት የተቀረጸ ነው።

ፕሮግራሙን ለማስጀመር በቅድመ እቅድ ዝግጅት ሂደት ወቅት ባለድርሻ አካላቶችን በመለየት የእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ፍላጎትና ከሆስፒታሉ የሚጠብቋቸው ውጤቶችን በመዳሰስ እንደ መነሻ እንዲወሰዱ መደረጉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ገልጸዋል፡፡

በእቅድ ዝግጅት ሂደቱ የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ ሲኒየር ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የችግር ልየታና አፈታት ዘዴ መከናወኑን ተናግረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች፣ ግቦች፣ የግቡ ማስፈጸሚያ ስልቶች፣ መለኪያዎች፣ የሚጠበቁ ውጤቶችንና ፈጻሚ አካላትን በመለየት ግልጽ የድርጊት መርሀግብር መቀመጡንም አስረድተዋል፡፡

በመርሐግብሩም ከሜዲካል ሴንተሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በሚታዩ ተግዳሮቶች ዙሪያ ውይይት መደረጉን ነው ዶክተር ሊያ የገለጹት።

“በተጨማሪም በሜዲካል ሴንተሩ ውስጥ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች የጤና ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሜዲካል ሴንተሩና ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ በጋራ በመሆን መፍታት የምንችልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተናል” ብለዋል ።

የጤና ሚኒስቴር በዚህ ዓመት አይኬርን ለማስጀመር ከ24 ሆስፒታሎች ጋር እየሰራ እንደሚገኝም መረጃዎች ያሳያሉ።