ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የዓሳ ማራቢያ ማዕከል አቋቁሞ እየሰራ ነው

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ዘመናዊ የዓሳ ማራቢያ ማዕከል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በዓሳ ሃብት አጠቃቀም ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የምክክር በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ እንዳሉት ማዕከሉ በጥናት ግኝት ላይ በመመስረት አርሶ አደሩ ትናንሽ ኩሬዎችን በነፍስ ወከፍ በማዘጋጀት በቤተሰብ ደረጃ ዓሳን እንዲያረባ ለማስቻል ነው።

ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን ጭምር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አካባቢው ለዓሳ ሃብት ልማት ምቹ የሆነ የውሃ አካል ፀጋን ተጎናጽፎ ሳለ በበቂ ሁኔታ ባለመመረቱ በርካታ ሆቴሎች የሚጠቀሙት ምርቱን ከሌላ አካባቢ እያመጡ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ለመቀየር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ዕቅድ ወጥቶ ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ በውሃ አያያዝ፣ ዓሳ ማስገርና ዘላቂነታቸውን ማረጋገጥ ላይ ምሁራን፣ ባለሙያዎችንና አርሶ አደሮችን አቀራርቦ ለመስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የዓሣ እርባታን ለማስፋፋት የሚያስችል የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ታፈሰ ማቴዎስ በበኩላቸው ሃገሪቱ ዕምቅ የዓሳ ሃብት ቢኖራትም ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱና የዕውቀትና የቅንጅት ክፍተት ምክንያት በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም ብለዋል።

ይህንን ለመቀየርና ዘርፉን ለማሳደግ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የዓሳ አረባብ ዘዴን ለማስፋፋት ማዕከል ማቋቋሙ ፈር ቀዳጅ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

እንደ አገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ትኩረት ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች መካከል ዓሳ ልማት ዋንኛው መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የባዮሎጂካል ሳይንስ ትምህርት ከፍል ተመራማሪና የማዕከሉ አስተባባሪ ዶክተር ካሳዬ ባልከው ናቸው።

ለዚህ ስኬት ዩኒቨርሲቲው ማዕከል አቋቁሞ ወደ ተግባራዊ ስራ መግባቱን ጠቁመው ባለፉት ስድስት ወራትም ከ80 ሺህ በላይ የዓሳ ጫጩቶችን በማዕከሉ በማርባት ለ150 ሞዴል አርሶ አደሮች ማከፋፈላቸውን ጠቅሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።