ሀገሬ-ዕድሜ ጠገቡ የጢያ ትክል ድንጋይ

በዛሬው “ሀገሬ” በተሰኘው ዝግጅት የጎብኝዎች መዳረሻ ስለሆነው ዕድሜ ጠገቡ የጢያ ትክል ድንጋይ እናስቃኛችኋለን። የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ ጢያ ከተማ ይገኛል።

እነዚህ ዕድሜ ጠገብ ትክል ድንጋዮቹ ቆይታ ከ700 እስከ 900 ዓመት እንደሚደርስና ከ12ኛው እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደተተከሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የአርኪዮሎጂ አጥኚዎች በግኝታቸው እንደሚጠቅሱት የጢያ ትክል ድንጋዮች ከሰሐራ በታች ከሚገኙ ትክል ድንጋዮች ከአክሱም ሐውልት ቀጥሎ ዕድሜ ጠገብና ቀዳሚ ነው።

ድንቅ የመስህብ መዳረሻ የሆነው የጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ የሚዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው በ1972 ዓ.ም ነው።

በመካነ ቅርሱ ግቢ ውስጥ 44 የቁም ትክል ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡ የትክል ድንጋዮቹ ተፈልፍለው አሁን ወደሚገኙበት ሥፍራ የተተከሉት ደግሞ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ከሚወስድ ርቀት በማጓጓዝ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የትክል ድንጋዮቹ ርዝመት ትልቁ አምስት ሜትር ሲሆን ትንሹ ደግሞ አንድ ሜትር ነው።

በእያንዳንዱ ትክል ድንጋይ ጀርባ ቅሪተ አካል እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በወቅቱ ቀብር ሲፈጸም በመካነ መቃብሩ ከነመገልገያ ቁሳቁስ ቀብሩ እንደሚካሄድ የአርክኦሎጂ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በመካነ ቅርሶች ላይ ጎራዴ፣ ባህላዊ ትራስ፣ እንሰት፣ ከበሮ እና ሌሎች የተለያዩ ምስሎች ይገኛሉ።

በወንድና በሴቶች ምስል እንዲሁም ዕድሜያቸውን በሚገልጽ መልኩ በትክል ድንጋይ መካነ ቅርሶች ላይ የተለያዩ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ስዕሎች ተቀርጾባቸዋል፡፡

የትክል ድንጋዮቹ የሚተከሉት ለታዋቂ ሰዎች ሲሆን በህይወት እያሉ የሠሩትን ጀብድና በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ተጽዕኖ ለመግለጽ እንደሆነም ነው የተለያዩ የጥናት መረጃዎች የሚያመለክቱት።

በተጨማሪም ድንጋዮቹ የሚተከሉት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 ላሉ ወጣቶች እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ።

ይህ ታሪካዊና ዕድሜ ጠገቡን መካነ ቅርስ ለመጎብኘት ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ጢያ ከተማ መዝለቅ ይጠበቅቦታል። ከርዕሠ መድናችን አዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ ከተማ በሚወስደው መንገድ 88 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ያገኙታል። ይጎብኙ አገርዎን ይወቁ መልዕክታችን ነው፡፡

ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ