በመዲናዋ ከ670 ሺሕ በላይ የመሬት ይዞታ መረጃን ዲጂታል ማድረግ መቻሉ ተገለጸ

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ጌታቸው

መጋቢት 23/2016 (አዲስ ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 670 ሺሕ 568 የመሬት ይዞታ ማህደሮች ከሙሉ መረጃዎቻቸው በዲጂታል ስርዓት መመዝገባቸው ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ጌታቸው እንደገለጹት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ውስጥ ባሉት ጽህፈት ቤቶቹ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የመስጠት፣ ህጋዊ ሰነድ ላላቸው ይዞታዎች ዋስትና እና እዳ የመመዝገብ ስራዎችን ተከናውነዋል።

በከተማዋ የመሬት አገልግሎትን በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችል የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተገልጿል።

በዋናው ቢሮ ከ50 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የሊዝ ውሎች፣ የተለያዩ የመሬት ውሳኔዎች እና ደብዳቤዎች በዲጂታል ስርዓት መመዝገባቸንው ነው ኃላፊው ያሳወቁት።

ባለፉት ስድስት ወራት የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በመሆን በመዲናዋ የሚነሱ የመሬት ችግሮችን ለመቅረፍ የሪፎርም ስራዎች ሲሰራ መቆየቱም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በመዲናዋ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የመደገፍ እና የማዘመን ስራ መሰራቱንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ባዶ ቦታዎችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምዝገባዎች መካሄዳቸውን አስታውቀዋል።

በግዛቸው ግርማዬ