ሁሉም የናይል አባል ሀገራት የሚተዳደሩበት ህጋዊ ማእቀፍ ያስፈልጋል ተባለ

ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

ነሐሴ 13/2014 (ዋልታ) ዘላቂነት ያለው የድንበር ተሻጋሪ ትብብር እውን እንዲሆን ሁሉም የናይል አባል ሀገራት የሚተዳደሩበትና የሚገዙበት ህጋዊ ማእቀፍ እንደሚያስፈልግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አመለከቱ።

30ኛው የናይል ሀገራት የሚኒስትሮች ካውንስል ጉባኤ በታንዛንያ እየተካሄደ ሲሆን በጉባኤው ላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የተፋሰሱ ሀገራት ትብብር በጠንካራ ህጋዊ መሰረት ላይ ለማንበር የጋራ ጥረት ተደርጓል።

በዚህም አራት የናይል ቤዝን ኢንሼቲቭን (NBI) አባል ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን (CFA) እንደ ብሔራዊ ህግ ማጽደቃቸውን ገልጸዋል።

የትብብር ማእቀፉን ያፀደቁ ሀገራትን ቁጥር ለማሳደግ የናይል ቤዝን ኢንሼቲቭን (NBI) ወደታለመለት የኮሚሽን ደረጃ እንዲሸጋገር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የትብብር ማዕቀፉን የማጽደቅ ሂደት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንዳልሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ ናይል ቤዚን ኢኒሽቲቭ (NBI) እንደ መሸጋገሪያ ማእቀፍ ሊያከናናቸው የማይችላቸው ስትራቴጂያዊ እና ሽግግራዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የናይል ተፋሰስ ልማት እና አስተዳደር ጉዳዮች ለማሳካት የትብብር ማእቀፉ መጽደቅ መሰረታዊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አስረድተው ሁሉም አባል ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆን እንዳለበትም መግለጻቸውን ሚኒስቴሩን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሸቲቭ (NBI) የሽግግር ማእቀፍ ሆኖ በዘጠኝ መስራች አባል ሀገራት የጋራ ራእይ የተመሰረተና ቋሚ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን እስከሚመሰረት የሽሽግር ማእቀፍ ሆኖ እንዲያገልገል ታስቦ መቋቋሙ ይታወቃል።