ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – ህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን የሚያስጠብቅለትን ወኪል ለመምረጥ የሚያበቃውን ካርድ ከወዲሁ በመውሰድ ሊዘጋጅ እንደሚገባ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አሳሰቡ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአውሲ-ረሱ ዞን ጭፍራ ወረዳ በመገኘት የመራጭነት ካርድ በወሰዱበት ወቅት እንደተናገሩት፣ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግልጽ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ያለምንም ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ነው።
ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ ጉዳዩ መንግስትና ምርጫ ቦርድ ብቻ የሚተው ሳይሆን ከህብረተሰቡ ጀምሮ የሁሉም አካላት ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እስከታችኛው አስተዳደር እርከን ድረስ አባላቶቻቸውን አስተባብረው በመስራት የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው ጠቅሰዋል።
ምርጫ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉትንና የተሻለ ይሰራልኛል ብለው ያመኑበትን ወኪል የሚሰይሙበት፣ አይጠቅመኝም ያሉትን ደግሞ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚያስተምሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
በዚህም በቀሩት ጥቂት ቀናት ህብረተሰቡ መብቱን የሚያስጠብቅለትን ወኪል ለመምረጥ የሚያበቃውን ካርድ በአቅራቢያው በተመቻቹ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት በመውሰድ ሊዘጋጅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማህበራትና በጎ-ፍቃደኛ ወጣቶች ህብረተሰቡ በህገ-መንግስቱ የተረጋጋጡለትን ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተገቢው መጠቀም በሚያስችለው ምርጫ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ህብረተሰብ በወሰደው ካርድ በመጠቀም ለሀገርና ህዝብ የሚበጁ ወኪሎችን ለመምረጥ ከተራ-አሉባልታና ውዥንብር እንዲሁም ስሜታዊነት ወጥቶ በሰከነና በሰለጠነ መንገድ የፓርቲዎችን የምርጫ ፕሮግራም በተገቢው በመከታተል ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርበታልም ብለዋል።
ለዚህም ክልሉ እንደመንግስት የሚጠበቅበትን ሃላፊነቱን በመወጣት ምርጫው ግልጽነትና ዴሞክራሲያነትን የተላበሰ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።