መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል ለሚያወጣቸው ህጎች ተግባራዊነት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ

ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚያወጣቸው ህጎች ተግባራዊነት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ የጥንቃቄ ተግባራትን በመተግበር ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋቶች መኖራቸውንም ዋልታ ያነጋገራቸው መምህራን እና ተማሪዎች ገልጸዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሠተ ጀምሮ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸው የሚታወቅ ቢሆንም ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተ ጉዳቱን እያደረሰ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ወረረሽኙ ከተከሠተበት ከመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወረርሽኙን መከላከል የሚያስችላትን እገዳዎችን መጣሏ የሚታወስ ሲሆን፣ ትምህረት ቤቶችን የመዝጋት እርምጃ በዋናነት የሚነሳ ነው። ይሁን እና ጥንቃቄ በተሞላ መንገድ የመማር ማስተማሩ ተግባር እንዲቀጥል መወሰኗን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች ወደ ቀድሞ ተግባራቸው መመለሳቸው ይታወቃል፡፡

ምንም እንኩዋን የመማር ማስተማሩ ስራ ከወትሮ በተለየ መልኩ በጥንቃቄ እንዲተገበረ አቅጣጫ  የተቀመጠ ቢሆንም  ያንን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ጉድለቶች መኖራቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የወረርሽኙ ጉዳት የከፋ ባልነበረበት ወቅት በየተቋማት ይደረግ የነበረው ጥብቅ የጥንቃቄ እርምጃዎች መላላታቸው ዛሬ ላይ በርካቶችን በሞት እንድናጣ ማድረጉንም እየተመለከትን ሲሉ በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የምርምር ዘርፍ አማካሪ ዶ/ር አበባው ገበየሁ ጠቁመዋል፡፡

ይህም ከህብረተሰቡ መዘናጋት ባለፈ የሚወጡ ህጎችን ተከታትሎ ለተግባራዊነታቸው ከመስራት ረገድ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን አመላካች እንደሆነና በዚህም የጤና ተቋማት እና ባንኮች የተሻሉ ሆነው መገኘታቸውን ገልፀዋል።

እያንዳንዱ ግለሠብ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ የጥንቃቄ ተግባራትን በማከናወን የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የገለጹት ዶ/ር አበባው፣ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ አገልግሎት ሠጪ ተቋማት የወጡ ህጎችን ባከበረ መልኩ ተገልጋዩን ማስተናገድ ቢችሉ ጥቅሙ የጋራ ነው ብለዋል።

(በድልአብ ለማ)