ህብረቱ ፆታዊ ጥቃትን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም እየሰራ መሆኑን ገለጸ

መስከረም 22/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ፆታዊ ጥቃትን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ከዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን በተደረገ ወይይት እ.ኤ.አ በ2025 በመላ ሀገሪቱ ፆታዊ ጥቃት እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም እና ዜሮ ለማድረስ መፈረሟም ተመላክቷል።

ይህንን ለማሳከትም የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ፆታዊ ጥቃቶችን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ፣ የማስተማር እና የማህበረሰብ ወይይቶችን በማካሄድ እና የወጣት ክበባትን በማቋቋም እየስራ ይገኛል ተብሏል።

በተጨማሪም ህብረቱ ከሌሎች ቤተ እምነቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ሁሉም ቤተ እምነቶችን ጨምሮ የሚመለከተው አካል በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች የሚታየውን ፆታዊ ጥቃት እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም ልሰራ ይገባልም ተብሏል።

ህብረቱ በዛሬው ዕለትም እስከዛሬ በተሰራው ስራ የተገኙ ውጤቶች ላይ እና የታዩ ክፍተቶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል።

በሜሮን መስፍን