ህወሓት በሰራዊቱ ላይ ለፈጸመው ጥቃት በሰራዊቱ ውስጥ ሆነው የቡድኑን ዓላማ ሲደግፉ በነበሩ ላይ ውሳኔ እየተሰጠ ነው

ሐምሌ 30/2013 (ዋልታ) – የምዕራብ ዕዝ ቀዳማዊ ወታደራዊ ፍርድ ቤት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰራዊቱ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ሲያደርስ በሰራዊቱ ውስጥ ሆነው የቡድኑን ዓላማ ሲደግፉ በነበሩ አባላት
ላይ ክስ በመመስረት ህጋዊ ውሳኔ እየሰጠ ነው።
ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል፡፡
እየተሰጠ ያለው የፍርድ ውሳኔ የህግ አግባብን ተከትሎ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማደራጀት፣ ምስክሮችን በመስማት እና ክስ በመመስረት እንደሆነም ተገልጿል።
በመከላከያ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የምዕራብ ዕዝ ምድብ ችሎት ሀላፊ ኮሎኔል ማርዬ እባቡ እንዳሉት፥ አሸባሪው ህወሓት ጥቃት ከመፈፀሙ ቀደም ብሎ በሰራዊቱ ውስጥ ሆነው ሰራዊቱን ተስፋ ለማስቆረጥና ከተልዕኮው ለማሰናከል በተደራጀ መልኩ በርካታ ከአሸባሪው ተልዕኮ የተቀበሉ አባላት ነበሩ፡፡
ኮሎኔል ማርዬ አባላቱ ገዳይ መርዝ ይዘው ሲንቀሳቀሱ በፍተሻ ስለመረጋገጡ፣ ለውጊያ የሚሆን ድርቆሽ ጭምርም ተይዞ በማስረጃነት ስለመቅረቡ፣ በማህበራዊ ሚዲያ የህወሀትን ፕሮፖጋንዳ ማስተጋባት ጨምሮ ከመስከረም 30 ቀን ጀምሮ መንግስት የለም በማለትም የህወሓትን አጀንዳ ሲያናፍሱ እንደነበር ተረጋግጧልም ነው ያሉት።
ውግንናቸውንም ለህወሓት በማድረግ ሰራዊቱን ከመንግስት ለመነጠል እንዲያማርር በማድረግ ከመስራታቸው በተጨማሪ ለውጡን ካለመቀበልም በላይ ስድብን ጨምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ማጣጣልም እንደነበርም ተገልጿል ።
የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ሲንቀሳቀስ አሸባሪው ህወሓት ተልዕኮ የሰጣቸው የነበራቸው ዝግጅት ከሰሜን ዕዝ ከደረሰው ጥቃት ያልተናነሰ ጉዳት ለማድረስ ዝግጅት ነበራቸውም ነው ያሉት ሀላፊው።
አባላቱ በህግ አግባብ መሰረት እንደየ ጥፋታቸው የይግባኝ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በአብዛኛው በሀገር ክህደት ወንጀል መከሰሳቸውን ጠቁመው በፍርዱም የሞትና የእድሜ ልክ እስራትን ጨምሮ ሌሎች ውሳኔዎች ተላልፎባቸዋል።
የምዕራብ ዕዝ ቀዳማዊ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኛ ሻለቃ ቶማስ ማቲያስ በበኩላቸው የዕዙ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በዕዙ ስር ካሉ ክፍሎች በተጨማሪ በሰሜን ዕዝ 5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ሰራዊቱን የወጉና እንዲወጋ የተባበሩትን በምርመራ በመለየት እና ክስ በመመስረት የፍርድ ውሳኔዎች እንደተሰጡ ጠቅሰው በሂደቱ ሰራዊቱ የሚያውቀውን ምስክርነት ለመስጠት ንቁ ተሳትፎ አድርጓል ብለዋል።
አብዛኞቹ ተከሳሾች ከሀገር ክህደት ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው ቢሆኑም ለሁሉም በችሎት ለታዩ ተከሳሾች በህጉ መሰረት ተከላካይ ጠበቃ እንደቆመላቸው ከመከላከያ ሰራዊት ፌስቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።