ህወሓት የታጣቂዎቹን አስከሬን ሰብስቦ በመውሰድ “ጅምላ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው ናቸው” በሚል የሀሰት ዘመቻ ጀመረ

ሐምሌ 27/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሓት የታጣቂዎቹን አስከሬን ሰብስቦ በመውሰድ “ጅምላ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው ናቸው” በሚል የሀሰት ዘመቻ ለመስራት እየተዘጋጀ መሆኑን መንግስት አስቀድሞ ያስጠነቀቀበት ጉዳይ አሁን ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡
ከሳምንት በፊት አሸባሪው ህወሓት በሁመራ ከተማ የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጸመ የሚል ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑን መንግስት በደህንነት ምንጮቹ አማካኝነት የደረሰበትን መረጃ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሀምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት በወቅታዊ መረጃ ማጣሪያ በኩል “ማስጠንቀቂያ በሚል በለቀቀው መረጃ መሰረት፤ “ጁንታው ከሰሞኑ የአማራ ልዩ ኃይልና መከላከያ በሑመራ ጭፍጨፋ እንደሚፈጽሙ በማኅበራዊ ሚዲያ ማሠራጨት እንደሚጀምር ዕቅዱ ያሳያል” ሲል አስቀድሞ አስጠንቅቆ ነበር።
በወቅቱም የመረጃ ማጣሪያው÷ ጁንታው የማይካድራ ዓይነት ጭፍጨፋ በሑመራ ከተማ ለመፈጸም ያሰበው ዕቅድ እንዳፈተለከበትና በዕቅዱ መሠረትም ከትግራይ ክልልና ከሱዳን አስርጎ በሚያስገባቸው ሠርጎ ገቦች አማካኝነት ጭፍጨፋውን እንደሚፈጽም ገልጾ ነበር።
ይህ መረጃ በተለቀቀ ማግስትም የአሸባሪው ደጋፊና ተመጽዋች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ‘‘በሁመራ ንጹሀን ተገድለው ወንዝ ውስጥ ተጥለዋል’’ የሚል አስቀድሞ የተቀናበረውን የሀሰት ዘመቻ መቀባበል መጀመራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
የወቅታዊ መረጃ ማጣሪያው በዚያው ቀን በለቀቀው ሁለተኛ ማስጠንቀቂያም÷ ቡድኑ በአፋር ግንባር በፈጠረው ትንኮሳ ከአፋር ልዩ ኃይልና ከመከላከያ ሠራዊት ምላሽ የተሰጠው መሆኑን በመጥቀስ ከአካባቢው ሲሸሽ ከ300 በላይ አስከሬኖች በሲኖ ትራክ ጭኖ ወደ መቀሌ መፈርጠጡን አስታውቆ ነበር።
በወቅቱ እንደተገለጸውም÷ በዚህ መልክ የሚያሸሻቸውን የሕጻናትና የሴቶች አስከሬኖች በአንድ መቃብር በመቅበር የጅምላ ግድያ የተፈጸመባቸው መቃብሮች አስመስሎ ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን የደኅንነት ምንጮችን ጠቅሶ መረጃ ማጣሪያው መግለጹ ይታወሳል።