ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ አፍሪካ በተፈጥሮ ሃብቷ ተጠቅማ ራሷን ማልማት እንደምትችል ማሳያ መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
ሦስት የግል ድርጅቶች ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የአራት ሚሊየን ብር የቦንድ ግዥ ዛሬ ፈጽመዋል።
አፍሪካ ውሃ የሁለት ሚሊየን ብር ቦንድ ግዢ የፈጸመ ሲሆን፤ ገደብ ኢንጂነሪንግ እና ኢትዮ ፍሎራ የተሰኙ የግል ድርጅቶች እያንዳንዳቸው የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል።
ጎን ለጎንም ሌሎች ባለሃብቶች የሦስት መቶ ሺ ብር የቦንድ ግዥ ለመፈጸም ቃል ገብተዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ድርጅቶቹ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ድርጅቶቹ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
“የአድዋ ድል የቅኝ ግዛት ማሰናበቻ ምልክት ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አፍሪካ በራሷ አቅም እራሷን ማልማት እንደምትችል ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በውጭ ሃይሎች የሚደርስባት ጫና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ጫና ቀላል ተደርጎ መታየት እንደሌለበትና በጋራ መመከት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ የተጀመሩ በርካታ ልማቶችን ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁሉም አንድነቱን በማጠናከር የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ማስመስከር እንደሚገባ ገልጸው፤ግድቡ ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ ሕዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍ በማሰባሰብና በማጠናከር አገሪቷ ከጥገኝነት እንድትላቀቅ ሁሉም በኃላፊነት መሥራት አለበት ነው ያሉት።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ የተቀመጠበት ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ የሉዓላዊነትና የመብት ተጠቃሚነት ማረጋገጫም መሆኑን ተናግረዋል።