ለሀገራችን የምንሰስተው አንድም ነገር የለም – የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር

ነሃሴ15/2013(ዋልታ) – ለሀገራችን የምንሰስተው አንድች የለም በማለት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች እና ስድስቱ ተጠሪ ተቋማት እና አንድ ፕሮጀክት መስሪያ ቤት የወር ደሞዛቸውን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ወጪዎች በመቀነስ 229ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊት አበርክቷል።

በዚህም መሠረት ከአመራሩ እና ሠራተኞች የወር ደሞዝ 16 ነጥብ 5ሚሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ከመስተንግዶ እና ከልዩ ልዩ ወጪዎች ተቀንሶ 213 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ለማግኘት ተችሏል ሲሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መስፍን አሰፋ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በጁንታው እኩይ ተግባር ከቀዬያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖችም ሰባት መቶ ኪሎ ግራም ግምት ያላቸው የህፃናት እና የአዋቂ አልባሳትና ጫማዎች ፣የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ 27ኪሎ የሚሆኑ የማይበላሹ የታሸጉ ምግቦችንም ማበርከቱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

ከገንዘብ ድጋፋ በተጨማሪ ደም የለገሡት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች እና አመራሮች በዚህም 270ዩኒት ደም መሠብሠቡም ተገልጿል።

ግንባር ድረስ በመዝመትም የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ አንድ ከፍተኛ አመራር እና ሁለት የቢሮ ሀላፊዎች እንዲሁም አምስት ሹፌሮች ከነተሽከርካሪያቸው መስሪያ ቤቱ መላኩንም ዶ/ር መስፍን ተናግረዋል።

የሀገርን ሠላም እያወከ ያለው ጁንታው የህወሓት ቡድን እስኪወገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

ሀገር ከሌሌ መሥራት ሆነ መኖር የማይታሠብ በመሆኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማቱ በሀገር ህልውና የመጣውን ጠላትን ለመመከት ሀገር በምትጠይቀው ሁሉ በመገኘት የበኩሉን አስተዋፅኦ በቀጣይነትም ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ገለፀዋል።

(በድልአብ ለማ)