ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ጉድለት ማነቆ መሆናቸው ተገለፀ

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የፖለቲካ አመራሩ የቁርጠኝነት ማነስና የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ጉድለት ማነቆ መሆናቸው ተገለፀ።

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ማነስና የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ችግር ተግዳሮቶች ናቸው ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ የተቋማት ሃላፊዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ከተቋማት ሃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብና በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉበት በመሆኑ የተቋማት ቅንጅትና የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከፍተኛ አቃቤ ህግ አቶ አቤል ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት የችግሩን ስፋት ለመቀነስ ፍልሰትን ከልማት አጀንዳዎች ጋር አቀናጅቶ መተግበር ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ ከታችኛው የፖለቲካ አመራር ጀምሮ የተቋማት ሃላፊዎችም ጭምር ችግሩን ለመፍታት የወጡ ፖሊሲዎችና ደንቦች ተግባራዊነት ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ስራ ትኩረት መስጠት አለባቸው።

ስራውን የአንድ ወቅት አድርጎ የመመልከት ዝንባሌዎችም አሉ ያሉት አቶ አቤል ችግሩን ለመፍታት ያልተቋረጠ ክትትልና የህገ-ወጦችን ሰንሰለት በጣጥሶ ስደትን እስከ ማስቆም መቀጠል አለበት ብለዋል።

የዘርፉን ችግር በቀላሉ ለመፍታት በቂ የሰው ሃይል፣ ቴክኖሎጂን መጠቀምና ከአጎራባች አገራት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።