የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ

የደቡብ ክልል የመስተዳድር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የመስተዳድር ምክር ቤቱን ውይይት በቪዲዮ ኮንፍረንስ መርተውታል፡፡

የመስተዳድር ምክር ቤቱም በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ከዚህ ቀደም ሲነሱ የነበሩ የከተሞች የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ከጥናት በኋላ በምክር ቤቱ ምላሽ እንደተሰጠባቸው ተሰምቷል፡፡

ለብዙ ጊዜያት የከተሞች ህዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ የከተሞች የፈርጅ ለውጥ ጥያቄን ጥልቅ ጥናት ተደርጎበትና መስተዳድር ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት አድርጎበት ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ከተሞቹ ወደ ፈርጅ 3 ከተማ አስተዳደር እንዲያድጉ መደረጉ በከተሞች መካከል ጤናማ የሆነ የውድድር መንፈስ በመፍጠር በሂደቱም የነዋሪውን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ፣ ከተሞች ከደረሱበት የእድገት ደረጃቸው አንፃር በመፈረጅ እየተመዘገበ ያለው እድገት ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ በማድረግ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ብሎም ከተሞች የገበያ፣ የአገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የቱሪዝም እና የትምህርት ማእከላት በመሆን ለአካባቢያቸው የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማእከል የመሆን ሚናቸውን እንዲጫወቱ ለማስቻል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በቀረቡ በኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ላይ መስተዳድር ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ 33 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን አጽድቋል፡፡

በዚህም በአገልግሎት ዘርፍ ሶስት በግብርናው ዘርፍ 15 እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍ 16 ፕሮጀክቶችን መርምሮ ማጽደቁን ደሬቴድ ዘግቧል፡፡