መስከረም 12/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት፣ ሙዚቃ፣ ትያትርና ስፖርት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓል የፀጥታ ስራውን የሚያግዙ 27 ሺህ 500 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ከሚገኙ የፖሊስ አባላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ያነሱት ኮማንደር ፋሲካ፣ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓል ያለምንም ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ከመዲናዋ ነዋሪዎች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በዓሉ ካለምንም የፀጥታ ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቅ ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፣ የመዲናዋ ነዋሪዎች ከመቼው ጊዜ በላይ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ በተለይ አጠራጣሪ የሆኑ ጉዳዮች ሲገጥሟቸው ጥቆማ በመስጠት አካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ እያደረጉት ያለውን ተግባር አድንቀው፣ ህዝቡ በሚያደርገው ጥቆማ በርካታ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ለአብነት አንስተዋል።
የፖሊስ አባላቱ የመዲናዋን ጸጥታ ለመጠበቅ ቀን ከሌት በተለየ ዝግጁነት እየሰሩ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ህብረተሰቡ የፀጥታ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉና አጠራጣሪና ጉዳዮች ሲመለከት በስልክ ቁጥሮች 011-1-11-01-11 ወይም በ991 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ማሳወቅ እንደሚችም ኮማንደር ፋሲካ ገልጸዋል።