ለመከላከያ ሠራዊት አባላት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ


መስከረም 19/2016 (አዲስ ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሠራዊት አባላት እና ለቋሚ ሲቪል ሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለሠራዊቱ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ መሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ለሠራዊቱ አባላት እና ቋሚ ሲቪል ሠራተኞች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ26 ሺሕ 673 ካሬ ሜትር ላይ ለ1 ሺሕ አባዎራዎች የሚተላለፍ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የሚገነባ መሆኑ ተገልጿል።

የፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብርጋዲየር ጀኔራል ደረጄ መገርሳ እንደገለፁት ለሀገር ህልውና አስጠባቂ ለሆነው መከላከያ ሠራዊት ደረጃውን የጠበቀ የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የዲዛይን ስራው ተጠናቅቆ ግንባታውም በተያዘው ዓመት ይጀመራል።

የጋራ መኖሪያ ቡሎኮቹ ከ16 እስከ 18 እንደሚደርሱና አንዱ ብሎክ እስከ G+12 የሚደርስ ባለ 1፣ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ ቤቶችን እንደሚይዝ ተመላክቷል።

የሠራዊቱ አመራሮች በቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቁጥር 1 እና 2 ሳይቶች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መጎብኝታቸውንም የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመለክታል።