ለመከላከያ ሰራዊት ከ1 ሺህ ላይ የቀንድ ከብቶችን ጨምሮ ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ሐምሌ 17/2013 (ዋልታ) – ከኦሮሚያ ክልል ዞኖች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በድጋፍ የተሰበሰቡ ከ1 ሺህ 60 በላይ የቀንድ ከብቶች በአፋር ክልል በግዳጅ ላይ ለሚገኘው ሰራዊት ተበረከቱ።

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሙሀመድ ጉዬን ጨምሮ ሌሎች ከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ነዋሪዎች  አፋር ክልል ጭፍራ አካባቢ በሚገኘው ግንባር ተገኝተው ከኦሮሚያ ክልል ዞኖች ለመከላከያ ሰራዊቱ በድጋፍ የተሰበሰቡ 475 ሰንጋዎች፣ 587 ፍየሎችና ከ150 በላይ ፍራሾችን ለመከላከያ ሰራዊቱ አስረክበዋል።

ህዝባችን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በጋራ በመቆም አስፈላጊው ድጋፍ የማድረግ ሂደቱ እንደሚቀጥል ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

የአይነት ድጋፎችን ይዞ ከአዳማ ከተማ የተንቀሳቀሰው ልዑክ በበኩሉ ሰራዊቱ የውጭ ጠላቶችን ጥቃት መቀልበስ የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን ተመልክተናል፣ አሸባሪው ህወሀት ከሰሞኑ በአፋር ክልል አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ለሚያካሂደው ትንኮሳ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።

ህወሀት በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ አባላትም ከኢትዮጵያ ህዝብ እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርለት ገልፀው ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሰው ጁንታም በቅርቡ ላይመለስ ይቀበራል ነው ያሉት።

የፌደራሉ መንግስት ለትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ መስጠትን እና ጊዜው ክረምት በመሆኑ የትግራይ አርሶ አደሩ ወደ ግብርና ስራው እንዲመለስ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ሰራዊቱ ትግራይን ለቆ እንዲወጣ ቢደረግም አሸባሪው ቡድን ይህንን በሰበዓዊነት ላይ የተመሰረተውን የተናጠል ተኩስ አቁም ተገዢ ሳይሆን ህፃናትን ጭምር ለጦርነት እየማገደ በመሆኑ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በጁንታው ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩም ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ በአፋር፤ በቆቦና በጎንደር አካባቢ ግንባሮች በግዳጅ ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት  የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

(በደረሰ አማረ)