ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ የሚያደርግበት ድረገፅ ይፋ ሆነ

ሐምሌ 17/2013 (ዋልታ) – በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባሉበት ቦታ ሆነው ድጋፍ የሚያሰባስቡበት ድረ-ገፅን መሠረት ያደረገ ፕላትፎርም ተዘጋጅቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን በ8100 በኩል ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት አሠራር የተዘረጋ ሲሆን በ3 የተለያዩ ዙሮች ከ252 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ ተነግሯል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶም ከ15 ቢሊየን ብር በላይ በቦንድ ግዢና በልገሳ ለግድቡ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ይሁንና ዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ የሚያደርግበት አሠራር ባለመዘርጋቱ ድጋፍ ማድረግ እየፈለገ ድጋፉን በሚፈለገው መጠን ማሰባሰብ ባለመቻሉ  ፕላትፎርም መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

ድረ-ገጹ ቀላልና አስተማማኝ ከመሆኑ ባሻገር ባሉበት አካባቢ ሆነው ለግድቡ ድጋፍ በማድረግ አሻራቸውን ማሳረፍ ለሚፈልጉ ሰዎች የተሻለ መንገድ እንደሚሆን ይታመናል፡፡

በድረ-ገፁ አማካይነት የሚሰባሰበው ድጋፍ ከብሔራዊ ባንክ በተሰጠ ፈቃድ በዘመን ባንክ ለግድቡ ግንባታ ወደከፈትነው የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲገባ የሚደረግ ሲሆን የሚውለውም ለታለመበት ዓላማ ብቻ ይሆናል ተብሏል፡፡

ይህ ፕላትፎርም ወደ www.mygerd.com ድረ-ገፅ በመግባት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡