ለምርጫው መሳካት አመራሩ ሊረባረብ ይገባል – አቶ ርስቱ ይርዳው

ግንቦት 27/2013 (ዋልታ) – ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ አመራሩ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

በወቅታዊ ጉዳይ፣ የመኸር ወቅት ግብርና ስራ፣ አረንጓዴ አሻራ እና መሰረተ ልማት ዙሪያ የሚመክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተጀምሯል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ እንዳሉት፤ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ አመራሩ በትኩረት መስራት ይኖርበታል።

አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት በየአካባቢው ለሰላም መደፍረስ የሚሆኑ ምክንያቶችን በመለየት አስቀድሞ የመከላከል ስራ መስራት አለበት ብለዋል።

ከዚህ በተጓዳኝም የመኸር እርሻ ስራ በተገቢው መንገድ እንዲከናወን ለአርሶ አደሩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋገጡ መረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፣ እንደ ሀገር እየገጠመ ካለው ተግዳሮት የተነሳ አመራሩ ብቃቱንና አንድነቱን በማጠናከር ተቀናጅቶ በመስራት ለውጡን ከዳር ለማድረስ መረባረብ እንዳለበት ተናግረዋል።

አመራሩ የውስጥና ውጭ ኃይሎችን ተጽዕኖ ለመቋቋም ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር በቅንጅት መስራት ተቀዳሚ ተግባር ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል። ለምርጫ መሳካት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ የክልልና ዞን ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ እንደሆነ ኢዜአ ዘግቧል።