ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – ለምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አባል ሃገራት ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች በሰላም ማስከበር ቅድመ ስምሪት ዙሪያ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ።
የከፍተኛ መኮንኖቹ ስልጠና ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ እየተሰጠ ሲሆን፣ በስልጠናው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ7 ሀገራት የተውጣጡ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች ተገኝተዋል፡፡ ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል።
ከኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ኮሞሮስ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬኒያ እና ብሩንዲ የተውጣጡ የፖሊስ መኮንኖች ስልጠናውን እየተሣተፉ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል ዳይሬክተር ብርጋዴል ጀነራል ጌታቸው ሽፈራው እንዳሉት፣ ስልጠናው ለቀጣናው የጋራ ሰላም፣ ዕድገትና የጋራ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖች በስልጠና መክፈቻ ላይ መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል 10 አባል ሃገራትን በውስጡ የያዘ መሆኑም ታውቋል።