በኖርዌይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሄደ

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – በኖርዌይ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ የበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በኖርዲክ ሀገራት የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ድሪባ ኩማ በበየነ መረብ መድረኩ ላይ በመገኘት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአድዋ ድል የጥንት አባቶቻችን በአንድነት በመቆማቸው የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና አንድነት እንዳስከበሩ ሁሉ፣ የዚህ ዘመን አድዋ የህዳሴ ግድብ ነው፡፡ በመሆኑም ዳያስፖራው ማህበረሰብ ለግድቡ ግንባታ በገንዘብ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና በአድቮኬሲ መስክም የተከፈተብንን አፍራሽ የሚዲያ ዘመቻ በመመከት በድጋሚ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ የአድዋ ድል ልያረጋግጥ ይገባል ብለዋል።

አምባሳደሩ በኖርዲክ ሀገራት ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በመጪው ወራት የሚካሄደው የሁለተኛ ምዕራፍ የውሃ ሙሌትን ተከትሎ አቅማቸው በፈቀደ ልክ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሰለሺ በቀለ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ እና ስለሶስትዮሽ የድርድሩ ሁኔታ ለታዳሚዎቹ ገለፃ አድርገዋል።

በተጨማሪም ደራሲና ገጣሚ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራም ለፕሮግራሙ ታዳሚዎች ከዕለቱ ዝግጅት ጋር ተያያዥነት ያለው አነቃቂ ንግግርና ጠቃሚ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

የገቢ ማሰባሰብ አጀማመርና ሂደቱን በሚመለከት በአስተባባሪ ኮሚቴ አመራሮች አማካይነት ለመድረኩ ታዳሚዎች ሰፋ ያለ መግለጫ የቀረበ ሲሆን፣ የመርሃ ግብሩን ዓላማ ተቀብለው ልገሳ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦችም በመድረኩ ላይ እውቅና ተሰጥቷል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንዳመላከተው፣ በአጠቃላይ እስከአሁን ድረስ በኖርዌይ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ደረጃ ለግድቡ ግንባታ የሚውል 300 ሺህ የኖርዌይ ክሮነር (አንድ ሚሊየን አራት መቶ አርባ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ብር) በስጦታ ተሰብስቧል፡፡

ይህም በኖርዲክ ሀገራት ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ለግድቡ ግንባታ በኤምባሲው አስተባባሪነት የተሰባሰበውን ሃብት መጠን 2 ሚሊየን 616 ሺህ 600 ብር አድርሶታል ነው የተባለው።