ለሰብአዊ ድጋፍ የሚሆን ተጨማሪ የምግብ እህልና ሌሎች ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል እየተጓጓዙ መሆናቸው ተገለጸ።
የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መኮንን ሌንጂሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተጨማሪ የምግብና ሌሎች ቁሳቁስ ወደ ስፍራው እየተጓጓዙ ነው።
በትናትናው እለት ድጋፉን የጫኑ ዘጠኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ መቐሌ መጓዛቸውን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በዚህም 2 ሺህ 900 ኩንታል ዱቄት፣ 280 ኩንታል መኮሮኒ፣ 438 ካርቶን የዱቄት ወተትና 200 ኩንታል ሩዝ አዳማ ከሚገኘው የኮሚሽኑ የእህል ማከማቻ መጋዘን ተጭኖ ወደ ስፍራው በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሰብአዊ እርዳታው እስካሁን ከ129 ሺህ ኩንታል በላይ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ወደ ስፍራው መጓጓዙንም ጠቅሰዋል።
“የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ቀጣይነት ይኖረዋል” ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በአገሪቱ ለ7 ወር የሚሆን የመጠባበቂያ የእህል ክምችት እንዳለም ተናግረዋል።