ለቦረና ዞን የድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ  ተደረገ

ጥቅምት 8/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል የኮንሶ ዞን አስተዳደር በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በበልግ ዝናብ መዘግየት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች የእንሰሳት መኖ ሳር ድጋፍ አደረገ።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳዊት ገበየሁ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የበልግ ዝናብ እጥረት ባስከተለው ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፣ በቦረና ህዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት የእኛም ጉዳት ነው ብለዋል።
በዚህም 18 የጭነት መኪና የእንሰሳት መኖ እና ሁለት ቦቲ ውሃ በድርቅ ለተጎዱ እንስሳት ድጋፍ አድርገዋል።
የኦሮሞ እና የኮንሶ ህዝቦች አንድ ናቸው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አስደንጋጭ የሆነውን የእንስሳት ሞት ለማስቀረት የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉም ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አብዱራሀማን አብደላ ለቦረና ወንድም ህዝቦቹ ድጋፍ በማድረግ ረገድ ኮንሶ ዞን የመጀመሪያ በመሆኑ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጃርሶ ቦሩ በበኩላቸው፣ ለተደረገላቸው የእንስሳት መኖና ውሃ ድጋፍ በቦረና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ለችግራችን ደርሳችሁ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረጋችሁ ወንድማማች ህዝቦች መሆናችሁን በፍቅር አሳይታችኋል ሲሉም መናገራቸውን ከኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።