ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በሆለታ ከተማ 11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ

ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ

መስከረም 6/2015 (ዋልታ) በሆለታ ከተማ በአንድ ሳምንት ጊዜ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ 11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ አቀባበል በኦሮሚያ ልዩ ዞን ዋልመራ ወረዳ እየተካሄደ ሲሆን ዋንጫው በሆለታ ከተማ ለአንድ ሳምንት ቆይታ ማድረጉ ተገልጿል።

የሆለታ ከተማ ከንቲባ አበራ ጋዲሳ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በከተማዋ በነበረው 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ 11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ ይህም ከእቅዱ በላይ 103 በመቶ መሆኑን አመላክተው ህብረተሰቡ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዋልመራ ወረዳ ማህበረሰብ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተቀብሏል፡፡

በአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የዋልመራ ወረዳ አስተዳዳሪ በቀለ ተስፋዬ ለዋንጫው አቀባበል ከመደረጉ በፊት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ገንዘብ ለማሰባሰብ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳዳሪ ግርማ ኃይሉ በአንድ ሳምንት ውስጥ 15 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸው እቅዱን ለማሳካት ህብረተሰቡ በቦንድ ግዥ ላይ መሳተፍ አለበት ብለዋል።

ህብረተሰቡም በታላቁ ግድብ ዋንጫ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ የቦንድ ግዢ እየፈጸመ ነው።

አስተር ጌታሁን (ከዋልመራ ወረዳ)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW