ለአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ ሊውል የነበረ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ተያዘ

ሐምሌ 30/2014 (ዋልታ) በህገ-ወጥ መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ክልል ሊገባ የነበረ ከ 1ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የውጪ ሀገር ዜግነት ያለው ተጠርጣሪ ጋር በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።

ተጠርጣሪው ገንዘቡን በኢንቨስትመንት ሽፋን ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ ለማስገባት የሰሌዳ ቁጥር አ.አ ኮድ 3-A29852 ቶዮታ ዶልፊን ተሽከርካሪ በኋላ ፍሬቻና በተለያዩ የመኪናው አካል ክፍሎች ደብቆ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል።

በፖሊስ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ለማወቅ እንደተቻለው የተያዘው ገንዘብ ለአሸባሪ የህወሓት ቡድን እኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሊውል እንደነበር አስታውቋል።

ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ የሽብር ተግባራትን ለመቆጣጠር የዜግነት ድርሻውን ይወጣ ዘንድ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።