ከ4ሺህ 300 በላይ ተሽከርካሪዎች እርዳታ ጭነው ትግራይ ገብተዋል – መንግስት

ሐምሌ 30/2014 (ዋልታ)  ከ4ሺህ 300 በላይ ምግብና ምግብ ነክ እቃ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

መንግስት በሶስት ወር ውስጥ 1 ሚሊየን 81 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል መላኩን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

መንግስት ቃል በገባው መሰረት ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ መላኩን አጠናክሮ መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን ከጥቂት ቀናት በፊት ወደ ስፍራው ያቀኑ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ፍርያማ ያልሆነ የቀደመ ትርክት ለማስተጋባት መሞከራቸው ተቀባይነት የለውም ተብሏል።

ወደ ክልሉ የሚላኩ የሰብዓዊ ድጋፎችን ለፖለቲካ ፍጆታ ከማዋል ይልቅ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች መድረስ እንደሚገባም ሰላማዊት ካሳ ጠቁመዋል።

መንግስት የሰላም አመራጮችን ገቢራዊ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጠቁሟል፡፡

በዙፋን አምባቸው