መስከረም 6/2014 (ዋልታ) እንግሊዝ ለኢትዮጵያ እስከአሁን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶዝ በላይ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ድጋፍ አደረገች፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በኢትዮጵያ የኢንግሊዝ አምባሳደር አሌክስ ካሜሮን እና የእናቶችና ህፃናት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም የኮተቤ ጤና ጣቢያ በኮቪድ -19 ክትባት ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የእንግሊዝ መንግስት በኮቫክስ የክትባቶች ጥምረት በኩል እስካሁን ለኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶዝ በላይ የአስትራዜኒካ ክትባት ድጋፍ በማድረጓ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ተወካይ አሌክስ ካሜሮን በበኩላቸው፣ የእንግሊዝ መንግስት በኮቫክስ የክትባቶች ዓለም አቀፍ ተደራሽ ለማድረግ ለጥምረቱ አባል አገሮች ለ20 በመቶ ዜጎች ክትባት የማዳረስ እቅድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ በጉብኝቱ ባዩት ነገር ደስተኛ እንደሆኑ እና በቀጣይም በኮቫክስ ዓለም አቀፍ ጥምረት የአስትራዜኒካ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡