ለ11 ዓመታት ዲያሌሲስ እያደረገ የሚገኘውን ወጣት ያገባችው አፍቃሪ

 

ኩላሊት እስከመስጠት የጸናው ፍቅር

መነሻውን ከቤተ – ክርስቲያን ያደረገ ፍቅር ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ቤተ – ክርስቲያን ውስጥ በተለያየ አገልግሎት ውስጥ ሆነው ተዋወቁ፡፡ አንድ ብሎ መፃፍ የተጀመረው ይህ የትውውቅ ምዕራፋቸውም እስከ ትዳር የቀጠለ የፍቅር መፅሐፍ ሆነ፡፡ መፅሐፉ ግን እንዲሁ የፍቅር ብቻ አልነበረም፡፡ አሳዛኝ ታሪክም አለው፡፡ ፅናትን ይዟል፡፡ እምነት ጎልቶበታል፡፡ ተስፋን ሰንቋል፡፡ በእሷ አፍቃሪነትና በእሱ ብርታት የተመሰረተ ድንቅ የፍቅር ታሪክ ነው፡፡ የሀና እና የቢኒያም ታሪክ። ወደ ታሪኩ…..

ቢኒያም አበራ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ከአራዶቹ መንደር ጨርቆስ ነው፡፡ ታዲያ ቢኒያም የተዋጣላት ሼፍ ነበር፡፡ በሚሰራቸው ምግቦች ብዙዎችን ጣት አስቆርጥሟል፡፡ የተራቡትን አጥግቧል፡፡ ከዚህ ባሻገር የሰፈሩ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ቋሚ አገልጋይ ነበር፡፡ ነገር ግን ቢኒያም ለረጅም ጊዜ ቆሞ የሰራው የምግብ ማብሰል ሙያ የጤና ችግር ፈጠረበት፡፡ ይህን የተገነዘበው ቢኒያምም ሌሎች ኮርሶችን በመማር ሙያ ይቀይራል፡፡ ግን አርፍዷል፡፡ ቢኒያም አርፍዶ ነበር፡፡ በአንድ የቀን ጎዶሎ አይኑ ይጋረድና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይገባል፡፡ በኋላም ሁለቱም ኩላሊቶቹ ከአገልግሎት ውጪ እንደሆነ ይነገረዋል፡፡ ዲያሌሲስም ይጀምራል፡፡ ይህ የሆነው እንግዲህ የዛሬ 11 ዓመት ገደማ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ትብብር ባንዲራቸው በሆኑት በሰፈሮቹ ልጆች እገዛ፣ በጓደኞቹ እንዲሁም ሰርቶ ባጠራቀማት ጥቂት ገንዘብ እየታገዘ የኩላሊት እጥበቱን ይቀጥላል፡፡ ቢኒያም ብርቱ ነው፡፡ ጠዋት እጥበት ተደርጎለት ማታ ቤተክርስቲያን ለማገልገል የሚሄድ ጠንካራ ወጣት፡፡ “ነገ መልካም ይሆናል” የሚል ተስፈኛ ወጣት ……….

 

ታዲያ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ በሁኔታው የምትደነቅ አንዲት ሴት አለች፡፡ ሀና መስፍን፡፡ እሷም እንደሱ የቂርቆስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ነች፡፡ ከዲያሌሲስ መልስ ወደ ቤተክርስቲያን ሲገባ ስታየው ትገረማለች፡፡ ተስፋው ያስቀናታል፣ እምነቱ ይገርማታል፣ ብርታቱ ይደንቃታል፡፡

በኋላም ተዋወቁ፡፡ ትውውቃቸውም ወደ ፍቅር ከፍ አለ፡፡ ሀናም ለእናቷ የሆነውን ሁሉ ነገረቻቸው፡፡ ይህን የሰማችው እናትም በሁኔታው ግር ተሰኘች፡፡ ብቸኛ ልጇ ሀና ናትና ነገሩ አስፈራት፡፡ ነገር ግን ምንም ከባድ ቢሆን እናት የልጅን ደስታ ነውና የምትሻው “ደስታሽ ደስታዬ” ነው ብላ ፈቀደች፡፡ የወደደችውን ወደደች፡፡

በዚህም ከአራት አመት ቆይታ በኋላ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም ትዳር መሰረቱ፡፡ አሁን አራት አመት በትዳር ቆይተዋል፡፡ በሰፈሮቹ ልጆች አጠራር “ከስተም” ዛሬም ዲያሌሲስ እያደረገ ነው፡፡ አሁን ግን ደከመ፡፡ ቢኒያም የድሮው ጥንካሬ ቀንሷል፡፡

በዚሁ ዙሪያ ሀና ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረገችው ቆይታ አሁን ቢኒ እየደከመብኝ ነው ትላለች፡፡ “ከዲያሌሲስ ሲመለስ ይደክመዋል፣ ምግብም አይበላም፤ በግድ የሚጎርሳት አንድ ሁለት ጉርሻም መልሳ ትወጣለች” ስትል ነው ያስረዳችን፡፡

በመሆኑም ሀና አንድ ኩላሊቷን ልትሰጠው ወስና ሙሉ ዝግጅቷን ጨርሳለች፡፡ በዚህም ለደጋግ ኢትዮጵያውያን ባስተላለፈችው መልዕክት “ያለንበትንና እያሳለፍን ያለውን ችግር በመረዳት የንቅለ ተከላውን ወጪ ሸፍኑልኝ” ስትል ትማፀናለች፡፡

እገዛ ማድረግ ለምትፈልጉ ወገኖች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ቁጥር 1000608474246 (ቢኒያም አበራ እና ሀና መስፍን) ወይም በስልክ ቁጥር 0913734394 (ቢኒያም አበራ) ደውለው ማግኘት የምትችሉ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

በእየሩስ ወርቁ