ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊነት ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

የካቲት 05/2013 (ዋልታ) – ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊነት መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ፍትሀዊ እንዲሆን፣ ውጤቱም በመራጮች፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በታዛቢዎች ተቀባይነት እንዲኖረው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡

ምክር ቤቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ሁለንተናዊ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ መንግስትን አሳስቧል፡፡

በህግ ማስከበር ዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸውና ችግር ውስጥ ላሉ አካላት የሚመለከተው አካል ሁሉ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪ በትግራይ ክልል ደርሷል ተብሎ በተለያዩ አካላት የተገለጹ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካላት በአስቸኳይ ተጣርተው ውጤቱ ለህዝብ እንዲገለጽ አሳስቧል፡፡

(በአካሉ ጴጥሮስ)