ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ ከ36.2 ሚሊየን በላይ መራጮች ተመዝግበዋል

ግንቦት 07/2013 (ዋልታ) – በተያዘው ወር ለሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ከ36 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የመራጮች ምዝገባ ትናንት መጠናቀቁን በፌስቡክ ገጻቸው የገለጹ ሲሆን የመራጮች ቁጥር መረጃው እስከ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
እስከ ግንቦት 4 በተካሄደው የመራጮች ምዝገባ የሴቶች ተሳትፎ 46 በመቶ መሆኑንም ገልጸዋል።
ቦርዱ ዛሬ የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር እያደረገ ነው።
በምክክሩ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን አስመልክተው ወይዘሪት ብርቱካን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የመራጮች መዝገባ ዘግይቶ መጀመርና፣ የምዝገባ ቁሳቁስ ለማጓጓዝ የትራንስፖርት እጥረት ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል።
ከክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጣቢያዎችን ዘግተው መጥፋት፣ መረጃ አለመስጠትና በተወሰኑ ጣቢያዎች ከመመሪያው ውጭ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን መዝግቦ መገኘትም ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል።
ችግሮቹ በየደረጃው እንዲፈቱ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደው የመራጮች ምዝገባው መከናወኑንም ተናግረዋል።
መራጮች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ምዝገባ እንዲያካሂዱ ለማድረግ ከ150 ሺህ በላይ አጭር የሞባይል የጽሁፍ መልዕክቶች መተላለፋቸውንም ገልፀዋል።
ቦርዱ በቀጣይ የምርጫው ሂደቶች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚያካሂደው ውይይት ቀጥሏል።
(በሄብሮን ዋልታው)