ሕወሓት የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ መከልከሉን መንግሥት አስታወቀ

ሰኔ 16/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ መከልከሉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ መንግሥት ሲሰራ መቆየቱን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር አስፈላጊ መሰረታዊ ድጋፎች በየብስም በአየርም ሲያጓጉዝ መቆየቱንም ያተተው መግለጫው አሸባሪው ቡድን ይህንን የመንግሥትን ጥረት ጥላሸት ለመቀባትና የሃሰት ፕሮፖጋንዳውን ለመንዛት ሲል ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰብአዊ ድጋፎች የሚግቡበትን ሂደት ለማስተጓጎል በተደጋጋሚ መሞከሩን መግለጫው አትቷል፡፡
በየብስ የሚገቡትን ሰብአዊ ድጋፎች ለትግራይ ሕዝብ እንዳይደርሱ መንገድ በመዝጋትና የእርዳታ ማስተላልፊያ ኮሪደሮች አካባቢ ትንኮሳ በመፈጸም ከራሱ የፕሮፖጋንዳ ስሌት ባሻገር ለትግራይ ሕዝብ ግድ እንደሌለው በተግባር እያሳየ መምጣቱንም ነው መንግሥት የጠቆመው።
በሽብር ቡድኑ በኩል የሚመጡ እንቅፋቶችን በመቋቋም መንግሥት አስፈላጊውን ያልተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ማድረጉ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና የተሰጠው መሆኑ ይታወቃል ፡፡
መንግሥት ያመቻቸውና በየቀኑ መድኃኒቶችና የህክምና ቁሳቁስ እንዲሁም የህጻናት አልሚ ምግቦች የሚላክበትን የአየር በረራ የሽብር ቡድኑ መከልከሉና ከትናንት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ ማድረጉ እንደታወቀም መግለጫው አስታውሷል።
መግለጫው ይህ የሕወሓት የሽብር ቡድን እርምጃ ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ የሃሰት ፕሮፖጋንዳው መሳሪያ ከማድረግ ውጪ ሌላ አላማ እንደሌለው ዳግም በተግባር የሚያረጋግጥ ነው ብሏል።
ይህንን የሽብር ቡድኑን ውሳኔ የአዠዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያወግዘው የክልከላውንም ምክንያት እንዲያጣራ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም መንግሥት እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ የትግራይ ክልል ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጠው።