የካቲት 30/2013 (ዋልታ) – በህግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ሥራ አቁሞ የነበረው መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከዚህ ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ ሥራ እንደሚጀምር በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ አስታወቁ፡፡
አቶ ሳሙኤል ሃላላ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በህግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ሥራ አቁሞ እንደነበርና ከህግ ማስከበር በኋላ መኪናዎቹ በየቦታው በመበታተናቸው የተነሳ ስራ ለማስጀመር አመች ሁኔታ ላይ አልነበረም፡፡
በፋብሪካው ላይ ጉዳት እንደሌለም መረጋገጡን የጠቆሙት አቶ ሳሙኤል፣ ለካልሽየም ካርቦኔት ማፈንጃ የሚውል ፈንጂ ከብሔራዊ ደህንነት እንዲላክ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ተጠይቆ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ይህ ተከናውኖ መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የሲሚንቶ እጥረት በዋናነት የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ የቀደመው መንግሥት ሲሚንቶ ምርት ኢንቨስትመንት ላይ ክልከላ ጥሎ እንደነበር፣ ክልከላው ከአገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በተያያዘ የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም መፍጠሩን ገልጸዋል።
ሰሞኑን የተፈጠረው የምርት እጥረት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመታዊ ጥገና፣ በብልሽት እንዲሁም በህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር በተያያዘ ሥራ በማቆማቸው የተነሳ እንደሆነ ጠቁመው፣ በመንግሥትና በግሉ ማህበረሰብ የሚሠራው የኮንስትራክሽን ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ እና በተለይ በለውጡ አመራር ፕሮጀክቶችን የማስጨረስ ስትራቴጅ ጋር ተያይዞ የበለጠ የሲሚንቶ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ የውጭ ምዛሬ ከማጣት የተነሳ የመለዋወጫ እቃዎችና የምርት ግብዓት እጥረት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ከመሄድ ጋር ተያይዞም ሥራ ላይ የሚሆኑበት ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መሄዱ ገበያ ላይ ለተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ዓመታዊ ጥገና በገባበት ጊዜ አደጋ ማጋጠሙና እስካሁንም ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ የማምረት አቅሙ አለመመለሱ፤ ሙገር፣ ዳንጎቴና ደርባ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የመሬት መንሸራተትና መሰነጣጠቅ እያጋጠማቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የምርት ሰዓታቸው ዝቅ እያለ መምጣቱ ለእጥረቱ ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት መንግሥት 85 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ሲሠራ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡ ከህዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ ለማድረስ ሲሠራ ቢቆይም እስካሁንም የፋብሪካዎቹን የማምረት አቅም 85 በመቶ መድረስ እንዳልቻለ አስታውቀዋል፡፡