መንግሥት ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸው አረንጓዴ አሻራቸው ያኖሩትን አመሰገነ

ነሐሴ 8/2014 (ዋልታ) መንግሥት የአገር ኩራት በሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸው አሻራቸው ያኖሩትን ሁሉ አመሰግናለው አለ።
የተቀመጠውን 20 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ግብ መምታት ብቻም ሳይሆን ከታቀደው በላይ ከ24 ቢሊዮን በላይ ችግኝ እንዲተከል ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸው የራሳቸውን አሻራ ያኖሩትን ሁሉ መንግሥት ማመስገኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
አገልግሎቱ 4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የአረንጓዴ አሻራ ስኬት ሀገራችን ድንቅ መስራት እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ነው ብሏል።
የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ/ም በይፋ ሲጀመር ለአራት ተከታታይ ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተጀመረ አገራዊ ፕሮጀክት ነበር ያለው አገልግሎቱ በዚህ መሰረት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላው ከተጀመረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በቢሊየን የሚቆጠሩ የዛፍ ችግኞች ተተክሏል፡፡
ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ብቻ 18 ቢሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በተያዘው የክረምት ወቅት ደግሞ ‟አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ቃል 6 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ከ6 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች በላይ መትከል ተችሏል፡፡
በያዝነው ክረምት የህብረተሰቡ ተሳትፎ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በዚህም 29 ነጥብ 46 ሚሊየን ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
በአጠቃላይ እስከአሁን ድረስ ከ24 ቢሊዮን፣ 2 ሚሊዮን ችግኝ በላይ ተተክሏል፡፡ በዚህ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ዓመት ከተቀመጠው 20 ቢሊዮን አገራዊ ግብ በላይ ተጨማሪ 4 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል ብሏል አገልግሎቱ።
መንግሥት ይህ በዐይነቱ የመጀመሪያ የሆነዉ ፕሮጀክት ከኢኮኖሚያዊና ስነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታዉም በላይ ያቀድነውን መጨረስ የምንችል፣ የመቻል አቅማችንን የሚያሳይ ታላቅ አገራዊ ድል ነው ያለ ሲሆን ይህ ስኬት አገራችን በድርቅ ብቻ የምትታወስ አገር ሳትሆን ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ድንቅ ዉጤት ማስመዝገብ የምትችል መሆንዋን ለዓለም የሚያረጋግጥ ጨምር ነዉ ብሏል።
የፕሮጀክቱ ዓላማ የደን መመናመን አደጋን ለመግታት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቋቋም፣ የሚገነቡ ትላልቅ ግድቦችን ከደለል ለመታደግ፣ የተፋሰስና ደን ልማትን ለማረጋገጥ ነዉ።
በዚሁ መሰረት ላለፉት ሶስት የክረምት ወቅቶች በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ስነምህዳራዊ ጠቀሜታዎች ተገኝተዋል፡፡
ለአብነትም በ2013 ዓ.ም በተደረገ ጥናት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 17 በመቶ ደርሷል፡፡ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዛፎችን ከመትከል ባሻገር ለምግብነት የሚውሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን በማልማት በምግብ ዋስትና ራሳችንን የመቻል አቅማችንን ማሳደግ ተችሏል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ ወንዞችን እና ምንጮችን በማጎልበት የበጋ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት እና የተፋሰስ ልማት በየአካባቢው እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ተጀምሯል፡፡ የአካባቢ መራቆትን እና የአፈር መሸርሸር መጠንንም በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በአነስተኛ መሬት ላይ ጥምር ግብርናን በማስፋፋት ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለውጪ ገበያ የሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን አምርቶ በመላክ የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ተጀምሯል።
የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ወንዞቻችን በደለል እንዳይሞሉም የአርንጓዴ አሻራ ልማቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል።
በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ ባሉት 120 ሺሕ የችግኝ ጣቢያዎች አማካኝነት በርካታ የሥራ እድልን መፍጠር መቻሉ የተገለጸ ሲሆን ከሁሉም በላይ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ የማህበረሰቡ ዛፍ የመትከል ባህል እንዲጨምር አድርጓል፡፡
የተለያዩ መሪ ቃሎችን በመጠቀም ሰፊ የህዝብ ንቅናቄዎችም መደረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ችግኝ በዘመቻ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግና ለውጤት ማብቃት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ግንዛቤ ማስፋት ተችሏል ተብሏል።
የአገር ኩራት የሆነዉ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት የተቀመጠዉን 20 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ግብ መምታት ብቻም ሳይሆን ከታቀደው አልፎ ከ24 ቢሊዮን በላይ ችግኝ እንዲተከል ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸዉ የራሳቸዉን አሻራ ያኖሩትን ሁሉ
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመስግኗል፡፡
በቀጣይ ለተተከሉ ችግኞች አስፈላጊዉን እንክብካቤ በማድረግ አገራዊ ግቦቻችን እንዲሳኩ ሁሉም የድርሻዉን እንዲወጣም መንግስት ጥሪዉን አቀርቧል፡፡